ቱሪዝም ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ፣ ለአንድ ሀገር ገፅታ ግንባታ ብሎም ለማህበራዊ መስተጋብሮች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የአለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በሀገራችን ለ34 ተኛ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደግሞ ለ42 ተኛ ጊዜ በመከበር ላይ የሚገኝ ሲሆን ይኸውም መርሀ-ግብር በጽዳት ዘመቻ ፣ በችግኝ ተከላ ፣ በብስክሌት ውድድር እንዲሁም በፓናል ውይይት ተከብሯል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር “ቱሪዝም ለሁንተናዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል የአለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በተለያዩ መርሀ-ግብሮች ሲካሄድ ከፍተኛ አስተዋፅዎ ለነበራቸው የሆቴል ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት የእውቅና መስጠት ፕሮግራም ከመካሄዱም በዘለለ የኪነ-ጥበብ ምሽትም ተካሂዷል ።
በዚሁም ፕሮግራም ላይ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ፣ የሆቴል ባለቤቶች ፣ ባለድርሻ አካላት ፣ የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በእለቱም የሰርከስ ትርኢት ፣ የግጥም ፣ የእውቅና ፕሮግራምና የተለያዩ የሀገራችን ብሄር ብሄረሰብ ሙዚቃዎች ቀርበው ምሽቱን አድምቀውታል ።
የአለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ያለው ፕሮግራምም በዛሬው እለት የሚቀጥል ሲሆን ከተማችን ድሬዳዋን በጉልህ በሚያስተዋውቀው በጥንታዊው ባቡር ላይ ጉብኝት የሚካሄድ ይሆናል ።


