በድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊሰ ኮሚሽን የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ 250 አባለት እና አመራሮች ወደ ቀጣይ የማእረግ እድገት ደረጃ ተሸጋግረዋል።

    በማእረግ ማልበስ ስነ-ስረዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊሰ ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ አለሙ መግራ የአስተዳደሩ ፖሊስ አሰራሩን አንድ እርምጃ ቀዳሚ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ህዝባዊነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
    ፖሊስ ህዝቡን በቅንነት የሚያገለግል ሙያውንና ማእረጉን የሚያከብር በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ቁመናው የተሟላ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት የበለጠ እንደሚሰራም ተናግረዋል።ተቋሙ ከተጣለበት ሙያዊ ሃላፊነት በተጨማሪ ማህበራዊ ግዴታውን በተለያዩ መንገዶች እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
    ኮምሽነር አለሙ አክለውም የድሬደዋ ፖሊስ በአስተዳደሩ አስተማማኝ የሆነ ሰላም እና ጸጥታ እንዲኖር በትጋት ሌት ከቀን ከመስራት በተጨማሪ በአገር ህልውና ማስከበሩ ሂደት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ያብራሩ ሲሆን ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሌጂን መሰረት ያደረገ አሰራርን በመተግበር ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ደረጃ ላይ እየተደረሰ መሆኑንን ጠቁመዋል።ሴት የፖሊስ አባላትን ወደ አመራርነት ደራጃ በማሳደግ እረገድ በርካታ በውጤታማነት የሚጠቀሱ ተግባራት መከናወናቸውን ኮምሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል።
    አሁን የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ቀጣይ የማእረግ እድገት የተሸጋገሩ 250 አባለት እና አመራሮች የተሰጣቸው የማእረግ እድገት ይበልጥ ለተሻለ ስራ እንዲተጉ ሙያቸውን እንዲያከብሩና ህዝቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ ተጨማሪ አቅም እና ሃላፊነት አብሮ እንዲቀበሉ የሚያደርግ እንደመሆኑ ሃላፊነታቸውን በዚሁ አግባብ መወጣት እናዳለባቸው ኮምሽነሩ የስራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
    በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ከድር ጁሃር የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽንና አባላት ለህዝብ መሰዋት በመሆን የአስተዳደሩ ሰላም እንዲረጋገጥ ሙያዊ ግዳታቸውን በብቃት እየተወጡ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
    በቀጣይም ድብቅ አላማ አንግበው ሰላምን ለማደፍረስ እንዲሁም ህገ -መንግስቱን እና ህገ -መንግስታዊ ስረዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ ለማክሸፍ ፖሊስ ከመቼውም በላይ በንቃት እንደሚንቀሳቀስ እምነቴነው ብለዋል።
    የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ቀጣይ የማእረግ እድገት የተሸጋገሩ አባለት እና አመራሮች በበኩላቸው የደረሱበት የማእረግ ደረጃ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በስነምግባርና በእውቀት የተመሰረተ አፈፃፀም ለማሰመዝገብ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።