የድሬ ገቢዎች ጤና ቡድን ” One Child for One Pack ” በሚል መሪ ሀሳብ በተለይም በከተማችን ድሬዳዋ ላይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች የሚውሉ የተለያዩ ለትምህርት መማሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ፣ ዩኒፎርሞች ፣ ጫማዎች በጎና ቅን አሳቢ ከሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ፣ ባለድርሻ አካላት ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞችን በማስተባበር ላለፍት አንድ ወራት ድጋፎቹ ሲሰበሰቡ ቆይተዋል ።
ይህንንም ተከትሎ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና የመስጠት መርሀ-ግብር የተካሄደ ሲሆን በዚሁም ፕሮግራም ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ከድር ጁሃር ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም መሀመድ ፣ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ እንዲሁም የካቢኔ አባላት ፣ ከፍተኛ የድርጅት ኃላፊዎችና የድሬ-ገቢዎች ስፖርት ክለብ አባላት እንዲሁም በዝግጅቱ የተጋበዙ የክብር እንግዶች በተገኙበት ለ 16 ትምህርት ቤቶች 1610 ደርዘን ደብተር ፣ ለ 200 ተማሪዎች ዩኒፎርምና ቦርሳ ፣ ለ120 ተማሪዎች ጥንድ ጫማ ርክክብ ተደርጓል፡፡
በእውቅና አሰጣጥ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ይህንን ድጋፍ ላደረገው የድሬ ገቢዎች ጤና ቡድን ያላቸውን ምስጋና አቅርበው በተለይም በከተማችን ድሬዳዋ ላይ በርካታ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ ብዙ ተማሪዎች መኖራቸውንና የድሬ ገቢዎች ጤና ቡድን ለሌሎችም ስፖርት ቡድኖች አርዓያ ሊሆን የሚችል በጎ ተግባር ማድረጉንም ወር ፈጡም ሙስጠፋ ጨምረው ተናግረው ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዋናነት ግብርን መሰብሰብ ቢሆንም በእንደዚህ አይነት የበጎ ስራ ተግባር ውስጥ መሳተፍ ደግሞ የበለጠ የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱሰላም መሀመድ ተናግረው ይህ ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ይህንን ስራ በራስ ተነሳሽነት ላከናወኑት የኮሚቴ አባላት ምስጋናቸውንም በእለቱ አቶ አብዱሰላም አቅርበዋል ፡፡
የድሬ ገቢዎች የእግር ኳስ ጤና ቡድን ላደረገው በጎ ተግባር በእጅጉ ደስ የሚልና የብዙ ተማሪዎችን ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ ላደረጋችሁት ድጋፍ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሙሉካ መሐመድ በትምህርት ቢሮና በተማሪዎቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።


