የናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር በድሬዳዋ አስተዳደር በከተማም ሆነ በገጠር በተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ስራዎች ላይ በስፋት በመሰማራት ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ። ፋብሪካው በድሬዳዋ አስተዳደር ለረጅም ጊዜያት በመብራት እጦት ሲቸገሩ ለነበሩ የኢጃነኒ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገና በ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የትራንስፎርመር ተከላና የመስመር ዝርጋታ ሙሉ ወጪ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው በዛሬው እለት በ 450 ሺህ ብር ወጪ 20 ለሚሆኑና ለችግር የተጋለጡ አረጋውያን ሙሉ የቤት ጥገና ስራውን ለመስራት ይቻል ዘንድ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዬ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋን ጨምሮ የከንቲባው ተወካይና የገንዘብ ልማትና ኢኮኖሚ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሱልጣን አልዪ እንዲሁም የናሽናል ሲሚንቶ ከፍተኛ አመራሮችና በጎ ፈቃድ ወጣቶች በተገኙበት ተጀምሯል ።
በመረሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት የናሽናል ሲሚንቶ በአስተዳደሩ በተለያዩ የልማት ስራዋች ላይ በመሳተፍ እያሳየ ያለው አስተዋጽኦ ይበል የሚያሰኝ ነው በማለት በቀጣይም ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ስራዋችን እንደ አስተዳደር አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል።
የናሽናል ሲሚንቶ አ.ማ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ወንዱ ንጉሴ በእለቱ ባስተላለፉት መልእክት ፋብሪካው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በቀጥታ እያከናወነ ካለው አስተዋፆ በተጨማሪ የሌሎች የልማት ዘርፎችን በመደገፍ የከተሞቻችንን ብሎም የሃገራችንን ህዳሴ እውን በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀው ለአብነትም ባለፈው በጀት አመት ለማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ከ25 ሚሊየን ብር በላይ መውጣቱንና በዚህም የህብረተሰቡን ለፋብሪካው ያለውን የእኔነት ስሜት ማጠናከር መቻሉን ገልፀዋል።
ፋብሪካው በቀጣይ አመትም ለማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ያለውን ተደራሽነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ ወንዱ ንጉሴ ያስታወቁት።


