በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኝውን የኮቪድ 19 ዴልታ ዝርያ ለመግታት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ጠቁመዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮቪድ 19 ስርጭት አሳሳቢ በሆነ መልኩ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸው በየቀኑ በአስተዳደሩ ከሚመረመሩት ውስጥ 20 በመቶ ቫይረሱ እየተገኘባቸው እንደሆነ በመሆኑም የጥንቃቄ እርምጃዎችን መተግበርና የመከላከያ ክትባትን መከተብ አማራጭ የለውም ብለዋል።
የመስቀል ደመራ /ከተራ/ በዓል በርካታ ምእመናን የሚታደሙበት ሃይማኖታዊ በዓል እንደመሆኑ ለኮቪድ 19 ስርጭት ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ስለሚችል ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር እራሱንም ሆነ ወገኖቹን ከቫይረሱ በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ የቢሮ ሃላፊዋ አሳስበዋል።
ቢሮው ከሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ወ/ሮ ለምለም ኮቪድ 19 በሽታን በመከላከሉ ሂደት የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን አውስተዋል።በመሆኑም ከዚህ ቀደም እያደረጉት እንዳለው ሁሉ ምእመኑ በዓሉን ሲያከብር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሆን ማስተማራቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የፀጥታ አካላትና ህግ አስከባሪዎች እንዲሁም በጎ ፍቃደኞች በበዓሉ አከባበር ሂደት የኮቭድ 19 ጥንቃቄን ከማድረግ አኳያ ታዳሚውን የማንቃት ስራ በማከናወን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ወ/ሮ ለምለም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ለመላው ህዝበ ክርስቲያን እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳቹ በማለት የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


