ላሳልያን የሽልማት እና የድጋፍ ማህበር ድሬዳዋ ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች 100 ሺ ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ::

    ላሳልያን የሽልማት እና የድጋፍ ማህበር ለ250 አቅመ ደካማ ተማሪዎች ከ100 ሺ ብር በላይ የሚሆን የትምህርት መረጃ ቁሶችን ዛሬ ደገፈ፡፡ ለከዚራ ት/ቤት፣ ለአባ ዮሀንስ ት/ቤት፣ ለገንደ ተስፋ ት/ቤት፣ ለምስለ እናት ት/ቤት፣ ለምስራቅ ጀግኖች ት/ቤት፣ ለአፈተ ኢሳ ት/ቤት፣ ለመድሀኒ ዓለም ት/ቤት፣ ለገንደ ገራዳ ት/ቤት፣ ለማሪያም ሰፈር ት/ቤት፣ እንዲሁም ለለገሀሬ ት/ቤት ለእያንዳንዳቸው ትምህርት ቤቶች 25 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል፡፡
    ድጋፉን ለተማሪዎች የሰጠችው የሀሮማያ ዩኒቨርሲት መምህርና የላሳልያን የሽልማት እና የድጋፍ ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነችው ወጣት ቃልኪዳን አዳነ ማህበሩ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብላለች፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመ ሶስት ዓመት መሆኑ ገልፃ የቀድሞ በብስራተ ገብርኤል እና በኖትሮዳም ት/ቤት ተምረው ያለፉ እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በሚገኙ ተማሪዎች እንደተቋቋመ ወጣት ቃልኪዳን በመርሀ ግብሩ ላይ ተናግራለች፡፡
    የ7ተኛ ክፍል ተማሪ ከሚል አብደላ የተደረገላቸው ድጋፍ ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግሯል፡፡ ሌላው የ8ተኛ ክፍል ተማሪ ዮሀንስ ጥላሁን አንድ ደርዘን ደብተር፣ ስክሪብቶ፣ እርሳስ፣ መቅረጫና ላፒስ መረዳቱ ከአንድ ቀን በኃላ የሚጀመረውን ትምህርት ለመጀመር ችግር እንደማይገጥመው ተናግሯል፡፡ ‹‹ሁሉም ሊደግፈን ይገባል፤ እንደልጆቹ ያለውን ሊያካፍለን ይገባል›› ብሏል፡፡