የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው የምስረታ ጉባኤው ለቀጣይ 5 ዓመታት ከተማዋን የሚመራ አዲስ አስተዳደር ዛሬ ይመሰርታል፡፡
ጉባኤው የምክር ቤቱን አፈጉባኤዎች የሚመርጥ ሲሆን የከተማዋን ከንቲባም ይሰይማል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው የካቢኔ አባላት ሹመትንም እንደሚያፀድቅ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ አስታውቀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን ተመራጭ የምክር ቤት አባላት ትላአንት ከሰአት ጀምሮ ስልጠና መስጠት ተጀመሯል፡፡
በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በመሰጠት ላይ ያለው ስልጠና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በንግግራቸው የስልጠናውን አላማ ሲገልፁ አዲስ ተመራጭ የምክር ቤት አባላት ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት የምክር ቤቱን የስነ-ምግባርና ፕሮቶኮል ለማስተዋወቅና ስለ ምክር ቤቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በነባር የምክር ቤት አባላት የተሰሩ ስራዎችን ለአዲስ የምክር ቤቱ አባላት በማስተዋወቅ በስራ ወቅት የታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማረም እንዲቻል በጥናት የተደገፈ ስልጠና መዘጋጀቱን አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ጠቁመዋል ፡፡
በመቀጠልም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የህግ አወጣጥ ክትትልና ቁጥጥር ሙያዊ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፈቃደ # ሶስቱ የመንግስት አካላት ምንነት ፣ ተግባርና ሃላፊነት ፣ የስራ ግንኙነት እና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤትን ህጋዊ ተግባርና ሃላፊነት እና ያለፉት የምርጫ ዘመኖች አፈጻጸምን በተመለከተ ለምክር ቤቱ አባላት የተዘጋጀ የመግቢያ ስልጠና በሚል ርእስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በተመሳሳይም በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባልና የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አብረሀም ሳህሉ #የምክር ቤት አባላት የአሰራር ስነ-ስረአትና ስነ-ምግባር በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
በቀጣይነትም የምክር ቤቱ ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ሃሳቦች በሚል ርእስ ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚቀርብና ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል ፡፡


