በአለማችን በአፍሪካ እንዲሁም ሀገራችን ኢትዮጲያን ጨምሮ የሰው ልጆችን ህይወት በመንጠቅ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የትራፊክ አደጋ በአመት 1.3 ሚሊዮን የሚሆን የሰው ልጆች ህይወትን ይነጥቃል ። ከዚህ ጋር ተያይዞም በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት ከጳግሜ እስከ ጳግሜ እንደርሳለን መርሀ-ግብር 13 ተኛው የእግረኞችና የብስክሌተኞች ቀን በምድር ባቡር አደባባይ ላይ ተከብሯል ።
በዚሁም መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት ወሮ ሰአዳ አዋሌ ነዋሪው ህብረተሰብ ከትራፊክ አደጋ እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ እራሱን ይጠብቅ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተናግረው ባለድርሻ አካላቶችም የበኩላቸውን አስተዋፆ እንዲወጡም ወሮ ሰአዳ በእለቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
በእግር ወይም በብስክሌት ትራንስፖርት ባህል አድርጎ እንዲጠቀም ለማስቻል ይቻል ዘንድም የሚመለከታቸው አካላት የራሳቸውን አስተዋፆ እንዲወጡም የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የትራፊክ ደህንነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ ተናግረዋል ።
የመርሀ-ግብሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች አጫጭር መንገዶችን በእግር ወይም በብስክሌት የመጠቀም ባህልን በማዳበር የራሳቸውን ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ በትራንስፖርት ሊያወጡት የሚችሉትን ኢኮኖሚ መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል ።


