መስከረም 30፣2014 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለብዙሃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ መሰረት በአገር አቀፍ እና በአስተደዳሩ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በነገው ዕለት እንደሚከበር የተከበሩ ወ/ሮ ፈትያ አደን የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ገልጸዋል ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ለ14ኛ ጊዜ “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት1/2014ዓ.ም ይከበራል፡፡የተከበሩ አፈ-ጉባዔዋ በመግለጫቸው ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ የአንድ አገር ዜጎች አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜትን የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና ስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀበረቁበት የአገራዊ አንድነትና ህብረት አርማና ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር በህግ መደንገጉን አስረድቷል ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው በአንድ በኩል 6ኛው አገር አቀፍ ብሄራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ዴሞክራሳዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ በምርጫው ውጤት መሰረትም በአስተዳደሩ አዲስ ምክር ቤት እና የመንግስት ምስረታ በተካሄደበት ማግስት እና በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባትና ብልፅግናን ለማምጣት አዲስ ምእራፍ በጀመርንበት ወቅት በመሆኑ ከባለፋት የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል አከባበር ልዩ ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል አገራችን የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እየተፈታተኑ ባሉበት ወቅት የሰንደቅ ዓላማ በዓሉን ማክበር፤ በጋራ በተቀናጀነ በተባበረ ክንድ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመመከትና ለመቀልበስ ፤ ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በባንዲራችን ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስ እለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት 14ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት እና በአስተዳደሩ በሚገኙት ሁሉም መንግስታዊና መንግታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች ፣በወታደራዊ ካምፖች እና በሌሎች ተቋማት በተመሳሳይ ሰዓት 4:30 ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም የሰንደቅ ዓላማ ቀን ተከብሮ እንደሚውል የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለብዙሃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል ፡፡
የድ/አስ/ም/ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
መስከረም 30/2014 ዓ.ም
ድሬዳዋ


