የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከሚያከናውናቸው የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎች ባሻገር በተለይም የነዋሪውን ህብረተሰብ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የተለያዩ ማህበራዊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በገንደ ተስፋ ለገ-ኦዳ አካባቢ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች በእጅግ የሚያገለግሉና ከ 450 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሶስት የቦኖ ውሀዎችን ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት አስመርቋል ።
በዚሁም የምረቃት ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ውሀ በእጅጉ እንደሚያስፈልገው ተናግረው ይህንንም ተከትሎ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላሰራቸው የውሀ ቦኖዎች የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ምስጋናቸውን አቅርበው በኮሚኒቲ ስራዎች ላይም አስተዳደሩ እገዛውን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሶስት የውሀ ቦኖዎችን 450 ሺህ ብር በሆነ ወጪ እንዳስገነባና ይህም የውሀ ቦኖዎች 1800 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ኡባህ አደም ተናግረው ዩኒቨርሲቲው በዋናነት የነዋሪውን ህብረተሰብ ችግር መፍታትን አላማ በማድረግ በቀጣይም ነዋሪውን በሰፊው በማወያየት የሚነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው እንደሚሰራም ነው ዶክተር ኡባህ አደም በእለቱ የተናገሩት ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ በተወሰነው መሰረትና ለጉዳዩ ቅድሚያ በመስጠት በአካባቢው የነበረውን የውሀ ችግር ከአስተዳደሩ ውሀ ልማት ጋር በጋራ በመሆን ሶስት ቦኖዎች ማሰራት መቻሉን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ለሚሰሩት የልማትና የፀጥታ ስራዎች ሁሉ ሳምንቱን ሙሉ ቀን ከለሊት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጎን በመሆን እንደሚሰራም የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ተናግረዋል ።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ከፍተኛ የውሀ ችግር እንደነበር ተናግረው አሁን ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢያቸው የውሀ ቦኖ በማሰራቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል ።
በፕሮግራሙ ላይም ከፍተኛ የአስተዳደሩና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የገንደ ተስፋ ለገ-ኦዳ አካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ለስራው መሳካት የላቀ አስተዋፆ ለነበራቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የእውቅና ሰርተፍኬት ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል ።


