የድሬደዋ ተወላጆች ዲያስፖራ ማህበር በአስተዳደሩ በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ ::

    በዋሂል ክላስተር ለገኦዳ ሚርጋ ገጠር ቀበሌ የሚገኙ ሁለት የሸራ ጣቢያ ትምህርት ቤቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት ያለመ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል
    በጉብኝቱ ትምህርት ቤቶቹ ያሉበት ሁኔታ ምልከታ የተደረገ ሲሆን አጅግ በጣም ለመማር ማስተማር ሂደት አመቺ ያልሆነ ደረጃ ላይ መሆናቸው ለመረዳት ተቸወሏል።
    ከጉብኝቱ በሗላ የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሙሉካ መሃመድ መንግስት በገጠሩ ክፍል የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በአንድ ቀበሌ ቢያንስ አንድ ትምህርት ቤት እንዲኖር በየአመቱ በርካታ ግንባታዎች እና የመሰረተ ልማት ማሟላት ስራ እያከናወነ ቢገኝም የገጠሩ ነዋሪ አሰፋፈር የተራራቀ ከመሆኑ አኳያ አሁንም ቢሆን በተለይ እድሜያቸው ከአስር አመት በታች የሆኑ ህፃናት ከመንደራቸው እሩቅ ተጉዘው ለመማር ግድ እየሆነባቸው ይገኛል ብለዋል።
    ህፃናቱ ከመንደራቸው እርቀው ለትምህርት መጓዛቸው ለተለያዩ አደጋዎች ስለሚያጋልጣቸው በአማራጭነት በሸራ ጣቢያ ትምህርት ቤት እንዲማሩ እየተደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ሃላፊዋ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር አመቺ አለመሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።መንግሰት የሸራ ጣቢያ ትምህርት ቤቶችን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለመገንባት በሂደት የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እያደረገ ቢገኝም በዋነኝነት በበጀት እጥረት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አለመቻሉን ወ/ሮ ሙሉካ አስረድተዋል።
    በዚህ መሰረት ችግሩ በመንግስት አቅም ብቻ መቀረፍ ስለማይችል የተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ በቀረበው ጥሪ መሰረት የድሬደዋ ተወላጆች ማህበር ጥሪውን ተቀብሎ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት በዋሂል ክላስተር በለገኦዳ ሚርጋ ገጠር ቀበሌ በሚገኙ ሁለት የሸራ ጣቢያ ትምህርት ቤቶች የመስጉብኝት ማድረጋቸውን ሃላፊዋ አብራርተዋል።ባዩት ነገርም ልባቸው እጅግ መነካቱን በቀጣይ በአጭር ጊዜ ምላሽ ለመስጠት በጉብኝቱ የተሳተፉ የማህበሩ አባላት ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል።
    በሌላ በኩል ባዩት ሁኔታ እጅግ ማዘናቸውን የገለፁት በጉብኝቱ የተሳተፉ የማህበሩ አባላት መንግስት በትምህርት ዘርፍ በሚያከናውነው ልማት ብቻ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ስለማይቻል የማህበሩ አባላትም ሆኑ ሌሎች በባህር ማዶ ያሉ የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆችን በማስተባበር የሸራ ጣቢያ ትምህርት ቤቶቹን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
    ትምህርት ለአገር እድገት ወሳኝ መሆኑን፣ ህፃናትን ማስተማር ትውልድን ማስተማር እንደመሆኑ መጠን ዘርፉን ለማገዝ ማንኛውም አካል ሆነ ግለሰብ ባለው አቅሙ በሃሳብም ሆነ በገንዘብ ብሎም በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው በመስ ጉብኝቱ የታደሙ የድሬደዋ ተወላጆች ዲያስፖራ ማህበር አባላት መልእክት አስተላልፈዋል።
    በድሬደዋ የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አክሊለ ታጠቅ ዲያስፖራው በአስተዳደሩ ልማት በተለያዩ መስኮች እያደረገ ካለው ተሳትፎ በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎትና በበጎ ተግባር ስራ ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።በቀጣይም ይህንኑ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ጥረት እንደሚያደርግ አቶ አክሊለ ጠቁመዋል።