በዛሬው እለት ከጠዋቱ 12:00 ሰአት ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር የቺኩንጉኒያ፣ የወባና ደንጊን በሽታ ለመከላከል የፅዳት ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን በዚህ የፅዳት ዘመቻ ላይም የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርና ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዋች በተገኙበት የፅዳት ዘመቻው ተካሄዷል።
የፅዳት ዘመቻው በየሳምንቱ አመራሩ ወቶ ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በማፅዳት ለህብረተሰቡ ምሳሌ ሆኖ ድሬደዋ ከዚህ ቀደም ወደ ምትታወቅበት ስሟ የመመለስ ስራ ተጀምሮ የሚቋረጥ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ስራ ሆኖ እንደሚቀጥል የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
በተለይም የፅዳት ዘመቻን ባህል በማድረግ ነዋሪው ህብረተሰብ በተለያዩ ጊዜያቶች አካባቢያቸውን ማፅዳት እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንዲሁም የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በፅዳት ዘመቻው ላይ ተናግረዋል ።
ነዋሪው ህብረተሰብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የሚገኙትን ቆሻሻዎች በማፅዳትና የአካባቢውን ፅዳት በመጠበቅ ከተለያዩ ወረርሽኝ በሽታዎች እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ለምለም በዛብህ ተናግረዋል ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረው የፅዳት ዘመቻ በቀጣይም በየሳምንቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በእለቱ ተገልፃል ።


