የኮቪድ 19ኝ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
ግብረ ኃይሉ በሳምንቱ የኮቪድ ስርጭትን አስመለክቶ ባደረገው ግምግማ ስርጭቱ ከመቀነስ ይልቅ መጨምር እንደታየበት አስታውቋል ፡፡
እንደ ግብረ ኃይሉ መረጃ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ ለ 2230 ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የናሙና ምርመራ ተደርጎላቸው 348 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ በደማቸው ተገኝቶባቸዋል ። በዚህ ሳምንትም የበሽታው የስርጭት መጠን በ16 ፐርሰንት የጨመረ ሲሆን አሁን ላይ 258 የኮቪድ-19 ታማሚዎች መመዝገባቸው በህክምና ማዕከላት ሲረጋገጥ ከነዚህም ውስጥ 220 በቤታቸው ውስጥ በመሆን እራሳቸውን እየተንከባከቡ ሲሆን 38 የሚሆኑ ታማሚዎች ደግሞ በድልጮራ እና በሳቢያን ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ያመላክታል ፡፡
በኮቪድ-19 በዚህ ሳምንት ብቻ 9 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ መሆኑ ከህክምና ማዕከላት የመጡ መረጃዎች አረጋግጠዋል ። የበሽታው ስርጭት በሀምሌ ወር 127 እንዲሁም በመስከረም ወር 848 ሰዎች በበሽታው የተያዙ በመሆናቸው ካለፉት ወራት ጋር ሲነጻጸር የ721 ብልጫ እንዳለው በምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ የሚመራው የኮቪድ መከላከል ግብረሀይል በሳምንታዊ ግምገማ መድረኩ አስታውቋል ።
የኮቪድ 19 ለመግታት በአስተዳደሩ የሚገኙ ሴክተሮችና የፌደራል ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ የተቀመጡትን የኮቪድ ፕሮቶኮሎች ጠብቀው ሊሆን እንደሚገባ የኮቪድ መከላከል ግብረ ኃይል አሳስቦ ህብረተሰቡም ኮቪድ ለመጀመርያጊዜ ሲከሰት የነበረውን ጥንቃቄ መልሶ እንዲተገብር ጠይቋል ፡፡
ከምንም በላይ ጥንቃቄ_አይለየን !!!
●መራራቅ ●መታጠብ ●መሸፈን ●መከተብ


