የዛሬ አመት ጥቅምት 24/2013 የህወሃት ሽብር ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ቀን “አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!” በሚል መሪ ቃል ጧፍ በማብራት ደመቅ ባለ ሁኔታ በድሬዳዋ ታስቦ ውሏል።
መርሃግብሩን በሀይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች በፀሎትና በቡራኬ ተጀምሯል።
በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የህወሃት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻ ያለውን እርምጃ ጥቅምት 24 በመከላከያ ሰራዊት ላይ መውሰዱ መቼም የማይረሳና አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥቁሩ ጥቅምት 24 የህወሃት የሽብር ቡድን ለሁለት አስርት ዓመታት ሲጠብቀው የኖረውን፣ ቤተሰቡን ሲደጉም እና ሲያግዝ የኖረውን የመከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በመፈጸም የሰራዊት አባላት፣ የጦር መኮንኖች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ንብረት የሆነው የጦር መሳሪያ በመዝረፍና ከባድ ጥቃት ማድረሱን በመግለጽ የአስተዳደሩ ወጣት አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ከመከላከያ ጎን በመቆም እንዲደግፍና እንዲዘምት በኮ/ል ዮናስ ሮባ በሀገር መከላከያ ሚ/ር የሀረሪ ክልልና የድሬዳዋ አስተዳደር የላይዘን ጽ/ቤት ኃላፊ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሽብር ቡድኑ የፈጸመውን ክህደት ለመቀልበስ በወሰደው እርምጃም የታገቱ የጦር አዛዦችን በማስለቀቅ፣ የተዘረፉ መሳሪያዎች እንዲወድሙ እና ገሚሶቹ ደግሞ እንዲመለሱ በማድረግ አገርን ከመፍረስ የታደጉ ሰራዊቶቻችን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ለመንካት በሽብር ቡድኑ የተወሰደው እርምጃ መቼም የሚረሳ ባለመሆኑ ይህ ቀን በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ መከላከያ ሰራዊታችን ከፍ ብሎ የሚታሰብበት ቀንም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በመርሃግብሩ ጎንለጎን ደሙን እየገበረ ላለው ሰራዊት የደም ልገሳ መረሃ ግብር በማከናወን ተካሂዷል።


