አሸባሪው የህወሀት ቡድን ሀገራችን ኢትዮጲያን የማፍረስ ግልፅ ጦርነት በማወጅ ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራውን በማካሄድ ላይ ይገኛል ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሀገርን የማዳን የክተት ጥሪና አዋጅ በሁሉም አካባቢ እየተካሄደ ስለሆነ ይሄንንም የክተት ጥሪ ምክንያት በማድረግ ” አካባቢህን ጠብቅ ወደ ግንባር ዝመት መከላከያክንና የፀጥታ ሀይሉን ደግፍ ” በሚል መሪ ቃል የሚከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ በዛሬው እለት ለሚዲያ ባለሞያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።
አንዱና ዋንኛው በዚህ ሀገር አቀፍ ሀገርን የማዳን ዘመቻ ጥሪ መሰረት የዛሬ አመት በሰሜን እዝ ላይ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት የተሰነዘረበት እለት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዛሬው እለትም ” አልረሳውም እኔም የኢትዮጲያ ሰራዊት ነኝ ” በሚል መሪ ቃል ፕሮግራሞች ይካሄዳሉ ።
የመጀመሪያው ፕሮግራምም የጁንታው አፈቀላጤዎች ለሊት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችንን ባጠቁበት እለት በ 45 ደቂቃ ውስጥ የሰሜን እዝን ደምሰናነዋል ብለው በሚዲያቸው ላይ ባወሩበት ወቅት ያንን አሰቃቂ ጥቃት ሁሉም ሰው ቀኑን እንዲያስታውሰው በማለት በዛሬው እለት ከቀኑ 4 ሰአት ላይ ለ 45 ደቂቃ ያክል በሁሉም የመንግስት ተቋማት ላይ የሚገኙ ሰራተኞችን ነዋሪዎች እጃቸውን ደረታቸው ላይ በማድረግ የአረመኔውን ድርጊት የማውገዝ ስነ-ስርአት እንደሚካሄድ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
አቶ እስቂያስ አክለውም ጥቅምት 24/2013ዓ.ም በማሰብ ጀግኖቻችንን በመዘከርና በማጀገን የተቃጣብንን ሀገር የማፍረስ አደጋ ህዝባዊ ትግል ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አኳያ በዛሬው እለት ከሰአት 11፡00 ሰአት ላይ በለገሀር አደባባይ የጧፍ ማብራት ስነ-ስርአትና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንዲከናወኑም ሀላፊው ተናግረዋል ።
በነገው እለትም ደግሞ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን አስመልክቶ የድሬዳዋ መላው ነዋሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ አካባቢውን እንዲጠብቅ በግንባር ልጆቹንም በማዝመትና እራሱም በመዝመት ሚናውን እንዲወጣና ከመከላከያ ጎን መሆኑን እንዲያስመሰከር የሚያደርጉ ሀገራዊና ወቅታዊ ውይይት መላው የከተማው ነዋሪዎችን ያሳተፈ ውይይት እንደሚካሄድ አቶ እስቂያስ ተናግረው የፊታችን አርብ አሸባሪውን የህወሀት ቡድን ሴራና አላማ የሚያከሽፍና የሚያወግዝ ብሎም ቅስም የሚሰብር አንድነትን የሚያሳይ ህዝባዊ ማእበል ያለበት ሰላማዊ ሰልፍ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ማህበረሰቦች በነቂስ ወተው ድሬዳዋ አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግና በዚሁ ላይም ጁንታውን የማውገዝና የሀገር መከላከያ ሰራዊታችንን ደግሞ የማጀገንና ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ለመዝመት ቃል የሚገባበት ሰላማዊ ሰልፍ የሚከናወን መሆኑንም አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረዋል ።
እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የክተት ጥሪውንም ታሳቢ በማድረግ ከአመራር ጀምሮ ወደ ግንባር በመዝመት የትኛውንም መስዋዕት ለመክፈል ብሎም በሎጂስቲክም ለመሳተፍ ዝግጅነቱን ያረጋገጠበት ሁኔታ መኖሩን አቶ እስቂያስ ታፈሰ ተናግረው እንደ ሀገር ሀገርን የማስቀጠል ሚና ለማስቀጠል የአውደ ውጊያ ልምድ ያለው የቀድሞ ስራዊት እንዲሁም እድሜአቸው ለትግል የደረሱ በሙሉ ጤነኝነት ላይ ያለ አካላት ሁሉ ለዘመቻው እራሱን አዘጋጅቶ ግዴታውን እንዲወጣ ሀገራዊ ጥሪ እየቀረበ ያለበት ሁኔታ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በከተማዋም ሰፊ የሆነ የሰራዊት ምልመላ የሚከናወንበት ስራዎች እንደሚሰሩም የቢሮው ሀላፊ ገልፀዋል ።
በተለይም ነዋሪው ህብረተሰብም ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመቀናጀት አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ካሉም ከፀጥታ ሀይሉ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመስራት ከተማችንን የመታደግ አካባቢያችንንም የመጠበቅ ሀላፊነት መወጣት እንደሚኖርበት አቶ እስቂያስ ታፈሰ አሳስበው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይና የፀጥታ ሀይሉ ላይ የሚነሱበትን የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በማክሸፍ ብሎም ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን በመለዋወጥና በማንኛውም መንገድ ከሰራዊቱ ጎን መሆን እንደሚገባም ነው የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ያስታወቁት ።


