በድሬደዋ አስተዳደር አሸባሪውን ጁንታ ለመቃወም እና ከጀግናው መከላከያ ሰራዊትም ጎን መሆናቸውን በተካሄደ ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከንቲባ ከድር ጁሃር ያስተላለፉት መልዕክት።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ያልተፈተነችበትና ችግሮች ያልገጠሟት ጊዜ የለም፡፡ ይሁንና የገጠሟትን ችግሮችና ፈተናዎች በጀግኖች ልጆቿ በድል ስትወጣ፣ለየትኛውም ፈተና ሆነ ችግር እንደማትረታ ስታሳይ ቆይታለች፤አሁንም ይህን ታላቅነቷንና አይበገሬነቷን በተግባር እያሳየች ነው፡፡
    ዘመናትን በድል አድራጊነት የዘለቀችው ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ ከሀዲው፣አረመኔውና የትውልድ ነቀርሳ የሆነው የህወሓት ቡድን ሃያልነቷን ላይፍቅ፣ከፅናቷ ላይነቀንቃት ከንቱ ልፋት እያደረገ ነው፡፡ ወትሮም እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ለመጣ እራሳችንን የምንሰዋ የጀግናዋ ሀገራችን የአብራኳ ክፋይ ነንና ይህን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገራችን ጫንቃ ላይ የምናላቅቅበትና ሰላም የሰፈነበት ህይወት የምንመራበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡
    በመሆኑም የዚህን ጁንታ ሴራና አሸባሪነት በማጋለጥ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትፈልገን ወቅት ላይ ነንና አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅና ፀጉረ-ልውጦች ሲያጋጥሙን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም እንዲሁም ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በትብብር መንፈስ በመስራት የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡
    ከምንም በላይ ደግሞ አቅሙ ያለን የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበል በሀገራችን ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተቀነውን ጁንታው የህወሓት ቡድንን ለመገርሰስ በመዝመት ከሀገራችን ጎን መቆም አለብን፡፡
    ህዝባችን ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ዕገዛ በታሪክ ማህደር ላይ ደምቆ የሚፃፍ ነው፡፡ የሀገር ደጀን፣ የሀገር ዋርካ የሆነው የመከላከያ ሰራዊታችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ህዝባዊነቱን ያሳየ፣ እያሳየም ያለ ነውና የህዝብ አለኝታነት ተለይቶት አያውቅም፡፡
    አሁንም ህዝባችን ይህን ለሰራዊቱ ያለውን አለኝታነትና ሁለንተናዊ ዕገዛ አጠክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
    ህዝባችን ወትሮም ቢሆን የወገኑ አጉራሽ የወገኑ አልባሽ ነውና ከሀዲውንና አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመገርሰስ እየተደረገ ባለው ተጋድሎ ለተፈናቀሉትና እየተፈናቀሉ ላሉት ወገኖቹ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
    ሀገራችንና ህዝቦቿን በታማኝነት በቅንነትና በትጋት ማገልገልም ከአውደውጊያ ውጪ ያለ ጀግንነት ነውና ሁላችንም በየተሰማራንበት የስራ መስክ ህዝባችንን በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል ጀግንነታችንን ማሳየት አለብን፡፡ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የበሬ ወለደ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉትን የሀገራችንን ሀቅ በማስተጋባት በማህበራዊ ሚዲያ አውደውጊያ ድል ለመንሳት መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡