10 ኛው ዙር የፅዳት ዘመቻ በዛሬው እለት ተካሄደ ፡፡

    የድሬዳዋ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የምትታወቅበት ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማን ለማድረግ ይቻል ዘንድ በተለይም የለውጥ አመራሩ ቁርጠኛ አቋም ይዞ በየሳምንቱ ቅዳሜ የፅዳት ዘመቻ ቀን አድርጎ በመወሰን ያለማቋረጥ በየሳምንቱ የፅዳት ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛል፡፡
    በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃርን ጨምሮ ምክትል ከንቲባ አቶ ሐርቢ ቡህ እንዲሁም የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የመንግስት ሠራተኞች በተገኙበት በ09 ቀበሌ በሚገኘው አዲሱ ሀይስኩል ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንዲሁም በአካባቢው ዙሪያ የፅዳት ዘመቻ አካሂደዋል፡፡
    በተለይም በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተደረገው የፅዳት ዘመቻ ዋንኛ አላማውም በአስተዳደራችን ህዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ከሚከበርባቸው ሁነቶች አንዱ የሆነው ሲምፖዚየም የሚከናወነው በትምህርት ቤቱ አዳራሽ በመሆኑና ለዚህም ይሆን ዘንድ ቅጥር ግቢውን ብሎም አካባቢውን ፅዱና ለእንግዶች ምቹ እንዲሆን ለማስቻል በማለም የፅዳት ዘመቻው ተካሂደዋል ፡፡
    የአስተዳደሩ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የፅዳቱ ተሳታፊ የሆኑት ከፍተኛ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች 16ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር በአስተዳደር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ዝግጅቶችን ተዘዋውረውም ተመልክተዋል፡፡
    ይህንኑም አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ እስቂያስ ታፈሰ ባስተላለፉት መልዕክት በአስተዳደሩ የተጀመሩ የፅዳት ዘመቻ ስራዎች ተጠናክረው በመቀጠል ድሬዳዋ ቀደም ሲል የምትታወቅበትን ፅዱና ውብ ከተማነቷ ተጠብቆ እንግዶቿን ማስተናገድ እንድትችል ሁሉም የድሬዳዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን እንዲወጡና ለዘለቄታውም በፅዳት ጉድለት ምክንያት ለሚመጡ በሽታዎች እራሳቸውን እንዲከላከሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡