በአስተዳደሩ የሚገኙ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ማህበረሰቡን ባግባቡ እና በተገቢው መልኩ በማገልገል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር አሳሰቡ፡፡

    ከንቲባ ከድር ጁሀር እንዲሁም በድሬደዋ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ድንገታዊ የስራ ላይ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
    የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንደሁም የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ድንገት በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመገኘት የአገልግሎት አሰጣጡ ሚገኝበትን ደረጃ ጎብኝተዋል፡፡
    ክቡር ከንቲባ ከድር በወቅቱ እንደተናገሩት ድንገት ሳያሳውቁ ያደረጉት ጉብኝት ተቋማት ለማህበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በመቃኘት መስተካከል ሚገባቸው ችግሮች ካሉ በፍጥነት ተስተካክለው ማህበረሰቡ የተሻለና የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል፡፡
    በቀጠይም መሰል ጉብኝቶችን በአስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ተቋማት ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ከንቲባው ፤ተቋማት ላይ ያሉ ሰራተኞችም የስራ ሰአትን በማክበር በአግባቡ ማህበረሰቡን እንዲያገልግሉ እና ተገልጋይን የሚያማርሩ አሰራሮች ከንግዲህ እንደ አስተዳደር ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡
    በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጉብኝታቸውም ተቋሙ ያለው የስራ አካባቢ አመቺነት እና ሳቢ መሆኑን አስታውቀው በአንዳንድ ክፍሎች ሚስተዋሉ የሰራተኛ መንጠባጠቦች ግን ለስተካከሉ እንደሚገባ ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ህዝብ ግንኙነት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡