16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት በአስተናጋጇ ድሬዳዋ በደም ልገሳ ተጀምሯል።
“ደም ያስተሳስራል” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሐራ ሁመድ እንደተናገሩት፤ ሀገርን ለማሻገር ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው ጀግናው መከላከያ ሠራዊት ደም መለገሱ በደም የተሣሠረ ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ነው፡፡
ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ወኪሎች የተለገሰው ደም አንድነትን በፀና መሠረት ላይ ይተክላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የደም ልገሳው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ኃይል እያስመዘገበ ለሚገኘው ድል የደስታ መግለጫ ስጦታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሣተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን፤ ደም በመለገስ የተጀመረው በዓል ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክርና ሀገር የማሻገሩን ዘመቻ ከግብ ለማድረስ መሠረታዊ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ታዳሚዎች ሀገርን እያሻገረ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት የሁሉም ብሔረሰቦች ተወካዮች ደም በመስጠት መተሳሰሩ ህብረ-ብሔራዊ አንድታችንን አፅንተን አገርን ለማሻገር የጎላ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
ከጀግናው ሠራዊታችን ጋር በደም መተሳሰርን በአንድነት የጀመርነውን ሀገር የማዳን ዘመቻና የደጀንነት ተልዕኮ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡
ከደቡብ ኦሞ የመጣው ወጣት ኢርኖይ ዶሮች ፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ ብቻ ሳይሆን በግንባር ከጎን በመሆን ኢትዮጵያን ለማሻገር በሚካሄደው እንቅስቅሴ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገረው።
16ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በድሬዳዋ በተለያዩ ዝግጅቶችና ሲምፖዚየም በመከበር ላይ ሲሆን የፌዴራልና የክልሎች አመራሮች በዓሉ ላይ ለመታደም ወደ ድሬዳዋ ገብተዋል።
ምንጭ፦DireMassMedia


