ጃን ትምህርት ቤት ለጀግናው የሀገራችን መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሀ-ግብር አካሄደ ።

    ጃን ትምህርት ቤት በተለይም በከተማ አስተዳደሩ ላይ የተማረ የሰው ኃይልን ከማፍራት አኳያ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ። ትምህርት ቤቱ ከሚሰጣቸው የመማር ማስተማር ተግባራት ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ ስራዎች ብሎም ሀገራዊ የሆኑ ድጋፎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
    ለአብነትም በትምህርት ቤቱ ለሚማሩና የመከላከያ ሰራዊት ልጅ ለሆኑ የ 50 % ቅናሽ በማድረግ አጋርነቱን ከማሳየቱም በዘለለ በሀገራችን በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ ከቤት ቅያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትንና ምግቦችን ማሰባሰብ ችሏል ። ጃን ትምህርት ቤት ኢትዮጲያዊ ማንነትን የሚያንፀባርቅ የንባብ ፣ የመዝናናትና የወዳጅነት ቀን በሚል ባዘጋጀው ባዛር ላይ ” ደማችን ለመከላከያ ሰራዊታችን ” በሚል መሪ ሀሳብ የደም ልገሳ መርሀ-ግብር አካሂዷል ።
    ከምንም ነገር በላይ ሀገር ሲኖር ማንኛውንም ነገር መስራት እንደሚቻልና ሀገር ከሌለ ግን ምንም ነገር መስራትም ሆነ ማከናወን እንደማይቻልና ለሀገራችን ሰላም የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉም የጃን ትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑት መምህርት በሻዱ ዳዲ ተናግረው በአንድ በኩል የመማር ማስተማር ስራቸውን በመስራት ጎን ለጎን ደግሞ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻልና ለዚህም ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን በማድረግ ላይ እንደሚገኙም መምህርት በሻዱ ተናግረዋል ።
    መምህርት በሻዱ ዳዲ አክለውም በተለይም ተማሪዎች የሀገራቸውን ባህል ፣ ታሪክ እያወቁ እንዲያድጉ እየተደረገ ከመሆኑም ባለፈ የተለያዩ ተግባር ተኮር ትምህርቶች በመሰጠት ላይ እንደሆነና በቀጣይም ለጀግናው የመከካከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም መምህርት በሻዱ ተናግረዋል ።
    በተለይም ህይወቱን ሳይሰስት ለሀገራችን ሰላም ቀን ከለሊት እየታገሉልን ለሚገኙት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይሆን ዘንድ የደም ልገሳ በማድረጋቸው መደሰታቸውን በደም ልገሳው መርሀ-ግብር ላይ ተሳታፊ የሆኑ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ወላጆች እንዲሁም በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተናግረው በቀጣይም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል ።