ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ድረስ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው በተለይም የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ከመሰብሰብ አንስቶ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በተወሰነው አቅጣጫ መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል በአስተዳደሩ በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ የግልና የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያሰባስቡ ማድረግ ተችሏል ።
የለገሀሬ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን እንዲሁም ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይሆን ዘንድ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በጋራ በመሆን ከ 1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ አልባሳት ፣ ምግቦችና ስንቆች ፣ የእርድ ከብቶችን ድጋፍ ማድረግ ችሏል ።
በዚሁ የድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርአት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወሮ ሙሉካ መሀመድ በተለይም መምህራን ከዚህ ቀደም ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከወር ደሞዛቸው ላይ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበርና ከዚህ ባለፈም በዛሬው እለት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የተለያዩ አልባሳት ፣ ምግቦችና ስንቆችን እንዲሁም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደግሞ የእርድ ከብቶች ድጋፍ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ወሮ ሙሉካ መሀመድ ተናግረው ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ ለነዋሪው ህብረተሰብ በታማኝነትና በቅንነት በማገልገልና በጋራ በመሆን ውጤታማ ስራን በመስራት የጠላትን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባም ነው ወሮ ሙሉካ መሀመድ በእለቱ የተናገሩት ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ የለገሀሬ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ጥሪውን ተከትሎ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ተፈናቃይ ለሆኑ ወገኖቻችን ላደረጉት ድጋፍ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደረጄ ፀጋዬ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ፣ ተማሪዎች ፣ መምህራን ብሎም የአካባቢው ነዋሪዎች በአስተዳደሩ በሚገኘው የምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል በመምጣት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሚገኝ በምስራቅ እዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል የሴቶች ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት ሌተናል ኮረኔል እታለም መኩሪያ ተናግረው ለዚህም ድጋፍ በሰራዊቱ ስም ምስጋናቸውን ሌተናል ኮረኔል እታለም አቅርበዋል ።
ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን ለመግለፅ ብሎም የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ይቻል ዘንድ የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ መቻላቸውን የለገሀሬ አንደኛና ሁለተኛ ደረጅ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀምዛ አህመድ ተናግረዋል ።


