በትናንትናው እለት በኢትዬጱያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ከአውሮፕላን ማኮብኮቢያው ግቢ ውጪ በተፈጠረ የኤሌክትሪክ ማሳ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ለተወሰነ ሰአት የአየር በረራ ተቋርጦም ቆይቷል፡፡
በኢትዬጱያ ስቪል አቬሽን ባለስልጣን ድ/ዳ/ቅ/ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ሺመልስ እንደገለጹት በትናንትናው እለት ከቀኑ 11 ሰአት ገደማ ከኤርፖርት ግቢ ውጪ የሚገኘው ዲ.ቪ.ኦ.አር የሃይል መቆጣጠሪያው ላይ በተፈጠረ ችግር ምክንያት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመሪ አሬስተር ላይ በተከሰተ ችግር እሳት በመነሳቱ የድርጅቱ እሳት አደጋ ግብረ-ሃይል አደጋውን ወዲያውኑ በቁጥጥር ሰር የዋለ ሲሆን አደጋው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ለተወሰነ ጊዜ የበረራ አገልግሎት መቋረጡን ተናግረው ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ወደ በረራ ማስተናገድ ስራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዬጱያ ኤርፖርቶች ድርጅት የድሬዳዋ አካባቢ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ተፈራ በበኩላቸው ለደንበኞቹ ደህንነት ሁልጊዜ የሚተጋው ድርጅታቸው ችግሩ እንደተከሰተ ወዲያው እርምጃ ተወስዶ እንደተስተካከለ ገልጸው በአሁኑ ጊዜ የበረራው አገልግሎት ያለምንም ችግር በተሳካ ሁኔታ ወደ ተፈለገው ቦታ እየተበረረ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል ፡፡
የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ጥላዬ ስለተከሰተው አደጋ እንደገለጹት የተከሰተው አደጋ በጣም አነስተኛ በመሆኑ በቀላሉ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ደንበኞች ያለምንም ስጋት አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በትናንትናው እለት በኢትዬጱያ ሲቪል አቬሽን ባለ-ስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ከአውሮፕላን ማኮብኮቢያው ግቢ ውጪ በተፈጠረ የኤሌክትሪክ ማሳ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ለተወሰነ ሰአት የአየር በረራ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡


