የየተቋማት ሀላፊዎቹ ይህን የገለፁት ለምእመናን በጋራ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶቻቸው ነው፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወሮ ሰአዳ አዋሌ እና በድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ይሄነው ሽፈራው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለአመታዊው የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በአል በሰላም አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን ለእንግዶችም እንኳን ወደ ውቢቷ የበረሀዋ ንግስት ድሬደዋ በሰላም መጣችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመሰልበአላት ወቅት በከተማዋ የተሽከርካሪ ፍሰቱ እንደሚጨምር ይጠበቃል ያሉት ኃላፊዎቹ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ትራንስፖርት እና ከትራፊክ አካላት የተውጣጣ ቡድን ከከተማዋ መግቢያ ደንገጎ ጀምሮ የከተማዋን ዋና ዋና መንገድ በመያዝ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቁጥጥር እና ክትትል ስራን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የህግ አካላት ብቻ ተግባር ውጤት ሊያመጣ አይችልም በተለይ ደግሞ አሽከርካሪዎች እና እግረኞች ህግን በማክበር በመንቀሳቀስ እና ከፍጥነት በላይ ባለማሽከርከር ነገን በጤና እንዲሻገሩ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
በተለይ በመሰል በአላት ወቅት መጠጥ ጠጥቶ ከማሽከርከር መቆጠብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡


