ህዳር 29/2014 ዓ.ም<<ወንድማማችነት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት>>በሚል መሪ ቃል ለ16ኛ ጊዜ በድሬዳዋ የተከበረው የኢትዮጰያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ከፍተኛ አስተዋፅኦና ትብብር ላበረከቱ ተቋማት የምስጋና ኘሮግራም በራስ ሆቴል እየተካሄደ ነው።

    “ወንድማማችነት ለሕብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ህዳር 29/2014 ዓ.ም በድሬዳዋ አስተዳደር አስተናጋጅነት የተካሄደው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደማቅ እና በተሳካ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ የተለያየ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናና እውቅና ለመስጠት በድሬዳዋ ራስ ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የአስተዳደሩ የተለያዩ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ፕሮግራሙን በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግር በማድረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲህያ አደን አስጀምረውታል፡፡
    ክብርት አፈ-ጉባኤዋ በንግግራቸውም ሀገራችን በአዲስ የለውጥ ምእራፍ ላይ በምትገኝበት ወቅት በአሉ በድሬዳዋ አስተናጋጅነት መከበሩ ድሬዳዋ የወደፊቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗን በግልጽ ያሳየ ሆኖ ማለፉን ጠቅሰዋል፡፡
    በአሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የድሬዳዋን አስተዳደራዊ የመብት ጥያቄዎች ለብሄር ብሄረሰቦችና ለከፍተኛ የፌዴራል የመንግስት ሃላፊዎች በሚገባ ማሳወቅ የተቻለበት በመሆኑ በአሉን ከአሁን በፊት እንደ አስተዳደር ከተከበሩ በአላት ሁሉ የተለየና ታሪካዊ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደሩ የአዲስ ምእራፍ አመራር በአሉ በደማቅ ሁኔታ ይከበር ዘንድ ያሳየው አንድነትና ህብረት ለቀጣይ አስተዳደራዊና ህዝባዊ የልማት ስራዎችን በትጋትና በብቃት የመወጣት አቅም እንዳለው ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም አመራሩና ህዝቡ በቅንጅት የሚሰሩት ስራ መጨረሻው ስኬትና ስኬት ብቻ እንደሚሆን በማመን ከትላንቱ ይልቅ የአስተዳደሩ አመራሮች ህዝቡ ከእኔ ምን ይጠብቃል በማለት በተሻለ ሞራልና መነቃቃት የህዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ወደ ስራ የተገባበት እና አመራሩ ከህዝብ የተቀበለውን አደራ የሚወጣበት ጊዜ መሆኑን አሳስበዋል ፡፡
    በመቀጠልም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር ንግግር ካደረጉ በኋላ በተሳካ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ የተለያየ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የሰርተፊኬትና ዋንጫ የመስጠት ስነ-ስረአት ተካሂዷል፡፡