ወደ ድሬዳዋ ለሚመጡ ዲያስፖራዎች ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይቻል ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መስራታቸውን በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ባንኮች አስታወቁ ።

    የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የአለማችን ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጲያዊያንና ትውልደ ኢትዮጲያዊያን እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጲያ ወዳጆች ወደ ሀገራችን ኢትዮጲያ እየገቡ ይገኛሉ ።
    በድሬዳዋ አስተዳደርም ከ አንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑ ኢትዮጲያዊያንና ትውልደ ኢትዮጲያዊያን ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ባንኮች ለዲያስፖራው ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ ።
    በተለይም ዲያስፖራዎች ሲመጡ ከኤርፖርት አንስቶ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበትን አማራጭ ከመፍጠር አንስቶ በከተማዋ ላይ የሚገኙ ባንኮች በሁሉም ቅርንጫፎቻቸው ለዲያስፖራው ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎትን በመስጠት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ባንኮች ባንኮች ዲስትሪክት ማናጀሮች ተናግረዋል ።
    ዲያስፖራው ወደ ድሬዳዋ በሚመጣበት ወቅት በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ከማድረግ አንስቶ በአስተዳደር ደረጃ ያሉ የኢንቨስትመንትና የስራ እድል ፈጠራ አማራጮች ላይም እንዲሰማሩ ማድረግና ዲያስፖራው ከሚኖርበት አካባቢና ካላቸው የህይወት ተሞክሮ አንፃር የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲያደርጉ በማድረግ ለሀገራቸው ዘላቂ ልማትና ብልፅግና የሚጠቅሙ ስራዎች ይሰሩ ዘንድም የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ የድሬዳዋ አስተዳደር የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አቤል አሸብር ተናግረዋል ።