በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ 9 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ተከስቶ ከነበረው ጦርነት በኋላ ፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስትን በሚያግዙበትና በሚደግፉበት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል ።
በውይይቱ ላይም በከፍተኛ ባለሞያዎች የተጠና እንዲሁም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የመንግስት ከፍተኛ አካላት ያፀደቁት ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በከተማዋ ላይ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበው ሰነድ ላይም የተለያዩ ሀሳብና አስተያየታቸውንም ሰተዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በውስጥም ሆነ በውጪ ያጋጠማት ከፍተኛ የሆነ አደጋ የህዝቦቿ አንድነትና ትብብር ውጤት ማምጣቱንና ከዚህ በኋላም ቢሆን ከነዋሪው ህብረተሰብ ፣ ከመንግስት እንዲሁም ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ከመግባባት ላይ መደረሱን የድሬዳዋ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዮናስ በትሩ ተናግረዋል ።
አቶ ዮናስ አክለውም በሀገራችን ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው የውስጥና የውጪ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በተለይም በውጪ ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ የሚደገፈው የፕሮፖጋንዳ ሂደት የነዋሪውን ህብረተሰብ አመለካከት ማዛባቱን ገልፀው ይህንን የመቀልበሱና የነዋሪውን ህብረተሰብ ሰላምና አንድነት የማረጋገጥ ብሎም የተጎዱ አካባቢዎችን የመደገፍ ስራ ከመንግስት ጎን በመሆን እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት በሚገባቸው ዙሪያ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል ።


