በፌዴራል ሰላም ሚንስትር አስተባባሪነት በተለያዩ ክልሎች በበጎ ፍቃደኝነት ከተሰማሩ 10 ሺ ወጣቶች ውስጥ በድሬደዋ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ ተሰማርተው ለ10 ወራት የቆዩ 98 ወጣቶች ዛሬ ተሸኝተዋል።
በሽኝት ስነስረአቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈቲሃ አደን የወጣቶቹ በጎ ተግባር ስራ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር የጋራ ሃገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር እረገድ ያለው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በአገር ሰላም አእሴት ግንባታ እንዲሁም ወጣቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ እውቀት እንዲቀስሙ መደረጉን አፈጉባኤዋ ጨምረው ገልጸዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አብደላ በከር ወጣቶች በአገራቸው ሰላምና ፈትህን ከማስፈን አንፃር የማይተካ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አውስተው ለ10 ወራት በድሬደዋ በመቆየት የበጎ ተግባር የፈፀሙ ወጣቶች በቀጣይ በዚህ እረገድ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።
ወጣቶቹ የነበራቸውን ቆይታ ሲያስተባብሩ የነበሩትና በድሬደዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ አሜ ወጣቶቹ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት መገንባት እንዲሁም የአእምሮ ህሙማን መንከባከብን ጨምሮ ባከናወኑት ተግባር በርካታ ማህበራዊ ጠቀሜታ ያለቸውን ስራዎች መፈፀማቸውን አብራረወተዋል።የወጣቶቹ በጎ ተገወባር በብር ሲተመን 12 ሚሊየን ብር እንደሚገመት አቶ ኢብሳ ጨምረው ገልጸዋል።
በበጎ ተግባር ስራው ላይ ከተሰማሩት ያነጋገርናቸው እንደገለጹት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ እንደመሆናቸው በቆይታቸው አንዱ የሌላውን ባህል እና እሴት መለዋወጥ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።በአገራቸው እድገት ላይ ወጣቶች ሊኖራቸው የሚገባውን የነቃ ተሳትፎን በተመለከተ እውቀት መቅሰማቸውንም ወጣቶቹ ገልፀዋል።
በቀጣይ ወደየመጡበት አካባቢ ሲመለሱ ያገኙትን እውቀት ለመሰሎቻቸው ለማካፈል እንዲሁም በበጎ ተግባር ስራ ላይ በዘላቂነት ለመሳተፍ እቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።
የአገራችን መፃኢ ተስፋ ወጣቶች እጅ ላይ እንደመሆኑ ሁላችንም ያለን አንድ አገር ኢትዮጵያዊያ እንደመሆኗ ወጣቶች ለአገራቸው ዘላቂ ሰላም እና ለዜጎች ሁለንተናዊ እድገት ካለማንም አነሳሽነት መስራት ይገባናል የሚል መልእክ ወጣቶቹ አስተላልፈዋል።
የብሄራዊ በጎ ፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ሁለተኛ ዙር እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል ።


