በቅድሚያ የእናት ሀገራችሁን ጥሪ በመቀበል፤ ከሀገር በላይ የሚቀድም ጉዳይ የለም ብላችሁ፤ ባህር አቋርጣችሁ፤ የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ሀገራችሁ ኢትዮጵያ፤ ብሎም የፍቅርና የሰላም ሰገነት ወደ ሆነችው፤ ዘወትር ልጆቿን በስስትና በአክብሮት ወደ ምትቀበለዋ ከተማ ድሬዳዋ እንኳን በሰላም መጣችሁ እላለሁ።
ሀገራችን ከድህነት ተላቃ ዜጎቿ በኢኮኖሚ የበለፀጉ እንዲሆኑ ከምታደርጉት አስተዋጽኦ ባሻገር፤ አገራችን በውስጥና በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ ሲደረግባት፤ ከወገናችሁ ጎን በመቆም ለአገራችሁ ደጀን በመሆን ላደረጋችሁት አስተዋፅኦ በራሴ፣ በድሬዳዋ አስተዳደርና በነዋሪው ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በአገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ አይነተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉና እያደረጉ ካሉ ዜጎች መካከል በውጭ አገራት ኑሮአቸውን ያደረጉ ዳያስፖራዎች በጉልህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “ሀገሬ ለእኔ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን ለሀገሬ ምን ሰራሁላት በል” የሚለውን የታላቁን የአሜሪካ መሪ ጆኔፍ ኬኔዲ አባባል፤ ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያኑ በቃል ሳይሆን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ለሀገሬ እኔ ነኝ ያለኋት ሲሉ በጭንቋ ጊዜ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆነው አኩርተዋታል፡፡
ድሬዳዋ የምስራቁ የንግድ፣ የኢንደስትሪና የኢንቨስትመንት ኮሪደር እንደመሆኗ መጠን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ከባቢ ያላት ሲሆን፤ በድሬዳዋ ኢንቨስት ማድረግ ለአልሚው አትራፊ፣ ለህብረተሰባችንም ከፍተኛ የስራ ዕድል የመፍጠር ትልቅ አቅም ነው፡፡ አስተዳደራችንም በአግልግሎት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጨምሮ በአጠቃላይ ከ35 በላይ አዋጪ የሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮችን በመለየት ዳያስፖራው በቀላሉ ወደ ልማት የሚገባበትን ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል፡፡
በመሆኑም የተከበራችሁ የድሬዳዋ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆናችሁ ዳያስፖራዎች በከተማችሁ የኢንቨስትመንት መስክ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንድታደርጉ ጥሪዬን እያቀረብኩ፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከእናንተ ጋር በቅርበት ከመስራት በተጨማሪ፤ በየትኛውም የልማት እንቅስቃሴአችሁ ሁሉ ከጎናችሁ እንደሚቆም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ


