ሲምፖዚየሙ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ተቀብለው፤ ከውጭ ሀገራት ወደ ትውልድ ከተማቸው ድሬዳዋ የመጡ የዳያስፖራ አባላት፤ በአስተዳደሩ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተዘጋጀ ነው፡፡
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፤ ዳያስፖራው እስካሁን ድረስ በድሬዳዋ ልማት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ያላቸውን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ወደ አስተዳደሩ ይዘው በመምጣትና፤ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል ፈጥረዋልም ነው ያሉት፡፡
አስተዳደሩ ከ35 በላይ አዋጪ የሆኑ አዋጭ መስኮችን በመለየት ዳያስፖራው በቀላሉ ወደ ኢንቨስትመንት የሚገባበትን ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል ያሉት ከንቲባ ከድር ጁሀር፤ የድሬዳዋ አስተዳደርም በሚሰማሩበት የልማት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከዳያስፖራው ጎን መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሲምፖዚየሙ የተሳተፉት የድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው፤ ለተወለዱባት ድሬዳዋ ሁለንተናዊ እድገት በሚችሉት አቅም ሁሉ የልማት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስታውቀው፤ በአሁኑ ወቅት በአስተዳደሩ እየታየ ለሚገኘው የለውጥ እንቅስቃሴ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ጨምሮ ድሬዳዋ ያፈራቻቸው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ምሁራንና የዳያስፖራ አባላት በሲምፖዚየሙ የተሳተፉ ሲሆን፤ የአስተዳደሩ መንግስታዊ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዬች፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


