ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ስፍራ የፅዳትና የማስዋብ ስራ አከናውነዋል።

    የድሬደዋ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የድሬዳዋ አገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ሃላፊ ሊቀ ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ተግባሩ ወንድማማቻዊ አንድንትን በማጎልበት አብሮነትን በማጉላት የሃይማኖት መቻቻልን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
    ምእመኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በአሉን በፍፁም ሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው መልእክት አስተላልፈዋል።
    በሌላ በኩል የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በዓሉ አብሮነታችንን በማጠናከር መልካም እሴቶቻችንን የምናጎለብትበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
    በተለይም ባለፉት አመታት የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላትን በማስታከክ በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የህዝቡን የቆየና የዳበረ የመከባበር፣ የመቻቻል ብሎም የወንድማማችነት መንፈስ እንዲላላ ከፍ ሲልም ግጭትና ሁከት እንዲፈጠር በተለያዩ አካላት ጥረት ሲደረግ እንደነበር መስተዋሉን ከንቲባው አውስተዋል።
    በመሆኑም የድሬደዋ ነዋሪ በሃይማኖት ሽፋን ጥፋት ለማድረስ ሙከራ የሚያደርጉ አካላትን እኩይ ሴራ በመገንዘብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀነናጀት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማስቻል ይገባል ሲሉ አቶ ከድር ጁሀር ጥሪ አቅርበዋል።
    ከበአሉ ጋር በተያያዘ ከክርሰትና እምነት ተከታዮች ውጪ ያሉ የሌሎች እምነት ተከታዮች የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በአሉን ከእምነቱ ተከታዮች ጋር በወንድማማችነት መንፈስ የማክበር የቆየና የዳበረ ልምዶችን ማስቀጠል ይገባልም ብለዋ!! ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር።
    የተለያዩ የእምነት አባቶች በስነ-ስርአቱ ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።