በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት የአስተዳደራችንን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለፀ ።

    የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወገኖቻችን እንዲሁም መስራት የሚችሉና እድሉን ያላገኙ አካላትን ወደ ፕሮጀክቱ በማምጣት በተለያዩ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ለአብነትም በአካባቢ ልማት ፣ በፅዳት ፣ በአረንጓዴ ልማት ፣ ሌሎች አነስተኛ መሰረተ ልማት ስራዎችን እንዲሰሩ በማድረግና ተጠቃሚ በመደረግ ላይ ይገኛል ። ከዚሁ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ በመጀመሪያ ምእራፍ የተሰሩ ስራዎች እንዲሁም በሁለተኛው ምእራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል ።
    የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት በአስተዳደራችን ለመጀመሪያ ጊዜ መተግበር የጀመረው በ 2009 ዓ.ም ሲሆን በከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮጀክትም የመጀመሪያ ምእራፍ ልማታዊ ሴፍቲኔት ትግበራ የነበረውም ከ 2009 እስከ 2013 ዓ.ም ነበረ ። ይህም ፕሮጀክት በመጀመሪያ ደረጃ ሲጀመር እንደ አስተዳደር በከተማ ውስጥ 80 ሺህ 400 መቶ የሚሆኑ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ መረጃዎችን በመሰብሰብና ከዚህ ውስጥም 55 በመቶ የሚሆነውን በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል በሚል የመጀመሪያው ምእራፍ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉንም የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግሯል ።
    ከተማችን ድሬዳዋ ላይ በሚገኙ 9 ቀበሌዎች ላይ 43 ሺህ 610 የሚሆኑ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በዚህ ፕሮጀክት እንዲታቀፍ የማድረግ እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር እንደተገባና ከነዚህ ውስጥም በመጀመሪያ ዙር 84 በመቶ የሚሆኑት በአካባቢ ልማት 16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ ይቻል ዘንድ ፕሮጀክቱ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን አቶ ሮቤል ተናግረው በመጀመሪያው ዙርም በ 2009 ዓ.ም በቀበሌ 05 ፣ 08 እና 09 ቀበሌዎች ላይ በአካባቢ ልማት 11 ሺህ 760 እንዲሁም በቀጥታ ድጋፍ ደግሞ 2 ሺህ 240 በአጠቃላይ 14 ሺህ ተጠቃሚዎችን በዚህ ፕሮጀክት ታቅፈው እንዲጠቀሙ ማድረግ መቻሉንም ነው አቶ ሮቤል ጌታቸው ያስታወቁት ።
    ይህ በእንዲህ እንዳለም በሁለተኛው ዙር በ 2010 ዓ.ም በ 04 ፣ 06 እና በ 07 ቀበሌዎች በአካባቢ ልማት 11 ሺህ 760 እንዲሁም ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ 2 ሺህ 460 በአጠቃላይ ወደ 14 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደተቻለና በሶስተኛ ዙር ማለትም ከ 2012 ጀምሮ በቀበሌ 01 ፣ 02 እና 03 ቀበሌዎች ላይ 13 ሺህ 112 በአካባቢ ልማት 2 ሺህ 498 ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንና ባለፍት ጊዜያቶች ውስጥም በዘጠኙም ቀበሌዎች ላይ በአካባቢ ልማት ላይ 36 ሺህ 632 ዜጎች በዚህ ሂደት ላይ እንደተሳተፍና 6 ሺህ 978 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ቀጥታ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ነው አቶ ሮቤል ጌታቸው የተናገሩት ።
    አቶ ሮቤል አክለውም በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ወደ 30 የሚሆኑ የጋራ መፀዳጃ ሽንት ቤቶች ፣ 2 የህዝብ መፀዳጃና ሻዎር ቤቶች ፣ 8 የመማሪያ ክፍሎችና አጥሮች ፣ የችግኝ መጠለያ አጥር ፣ 50 የሚሆኑ የመንገድ ዳር ቆሻሻ ማጠራቀሚያና ሌሎች በርካታ ስራዎች በልማታዊ ሴፍቲኔት መሰራታቸውን አቶ ሮቤል ተናግረዋል ።
    በሁለተኛው ምእራፍ በአስተዳደራችን በሚገኙ 6 የከተማ ቀበሌዎች ማለትም 04 ፣ 05 ፣ 06 ፣ 07 ፣ 08 ፣ 09 ላይ ልማታዊ ሴፍቲኔቱ ተግባራዊ እንደሚሆንና በዚሁም ዙር 6 ሺህ 253 የሚሆኑ አባዎራና እማዎራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ይህንንም ስራ ለማስጀመር ይቻል ዘንድም የድሬዳዋ አስተዳደር ከፌደራል ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመተባበር የፊታችን ቅዳሜ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር እንደሚካሄድና በዚሁም መርሀ-ግብር ላይም ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሆኑ ሚኒስትሮች ፣ ሚኒስትር ዲኤታዎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው 11 ክልሎች ላይ የሚኖሩ ከ 200 በላይ ሰዎች ፣ ከየቀበሌው የተውጣጡ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በመርሀ- ግብሩ ላይ እንደሚታደሙም ነው አቶ ሮቤል ጌታቸው በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ያስታወቁት ።