በድሬደዋ የታክሲ ትራንስፖርት የታሪፍ ክለሳ ተደረገ የታሪፉ ክለሳው ማህበረሰቡን እና አሽከርካሪውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መከለሱ ነው የተጠቆመው።

    በድሬደዋ ለረጅም አመታት የታክሲ አገልግሎት የታሪፍ ክለሳ ይደረግ እሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።
    ለዚህም በአሽከርካሪው ዘንድ ነዳጅ እና መለዋወጫዎች መጨመር ለጥያቄያቸው እንደ መነሻ ሆኖ ይጠቀሳል።
    የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህዝብ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አደረጃጀት ስምሪት ዳይሬክቶሬት በበኩሉ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ከትራፊክ ፖሊስ ከታክሲ ማህበራት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አዲሱን የከተማ ታከሲ ታሪፍ በመከለስ ይፋ አድርጓል። የዳይሬክቶሬቱ ዳሬክተር አቶ ተፈራ ነጋ እንደተናገሩት ታሪፍ ማሻሻያው እንደሀገር እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ
    ዋጋ መነሻ በማድረግ እና የተጠቃሚውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ባማከለ መልኩ መሰረት አድርጎ መከናወኑን ጠቁመው በዚህም በኪሎሜትር 0.50ሳንቲም ጭማሪ ሊደረግ ችሏል ነው ያሉት።
    ለአብነትም ያህል ቀደም ሲል ከሰኢዶ ሼል በሶስት ኪሎሜትር ሶስት ብር የነበሩ ርቀት አምስት ብር ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል።
    ሌላው ረጃጅም ርቀት ሆነው አስቸጋሪ የመንገድ ርቀት ላይ ያሉትን ታሪፉ ቀድሞ ከነበረው መጠን ማሻሻያ ሲደረግ አንዳንድ መስመሮች ላይ ቀደም ሲል በወጣው ታሪፍ እንዲቀጥል መደረጉን ጠቁመዋል።
    የወጡ ታሪፎችን በአግባቡ እንዲተገበሩ ቁጥትራችንን እናጠናክራለን ያሉት አቶ ተፈራ ማህበረሰቡ ከስር ከተዘረዘሩት ታሪፍ ውጭ ሲጠየቅ ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ሊያሳውቅ እና መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባ እንደሁም አሽከርካሪውም በተቀመጠው ታሪፍ በማገልገል ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
    እንደሁም ማንኛውም አሽከርካሪ በተሰጠው መስመር መሰረት በተቋሙ ቢሮ ቁጥር 3 ድረስ በመምጣት አዲሱን ታሪፍ በመውሰድ ግልፅ በሆነ ቦታ ላይ በማንጠልጠል አገልግሎቱን እንዲሰጥ ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ ይህን ሳያደርግ የተገኘ አሽከርካሪ ላይ በደንብ መተላለፍ አስፈላጊውን አስተማሪ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ተናግረዋል።