ኮሚቴው፣ በህገወጥ ንግድ በቂ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አሳሰበ፤

    ዜና ፓርላማ ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በህገ ወጥ ንግድ ላይ በቂ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
    ኮሚቴው ሰሞኑን በድሬ ዳዋ ከተማ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት፤ በድሬ ዳዋ ከተማ እና አካባቢው ከፍተኛ የህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ እንደሚካሄድ እና የቁጥጥር ስራውም ዝቅተኛ እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡
    ቋሚ ኮሚቴው ከንግድ እና ማህብራት ዘርፍ ምክር ቤት ተወካይ አባላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ የህገወጥ ንግድ ከፍተኛ ጫና እያሳሣደረ እንደሆነ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ተቀናጅተው ከመስራት አንጻር ውስንነት የሚታይባቸው እንደሆነ አረጋግጧል ።
    ህገውጥ ንግድ ከሚካሄድባቸው ምርቶች መካከል ጫት እና ነዳጅ ከፍተኛውን ደረጃ እንደሚይዙ ኮሚቴው ያረጋገጠ ሲሆን ችግሩን ለመቀነስ የቁጥጥር ስርዓቱ መጠናከር እና መዘመን እናዳለበት አመላክቷል፡፡
    የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካይ አባላት ዘርፉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ድጋፍ እየተደረገለት እንዳልሆነ እና ችግሮቸን ለመቅረፍ ያለው ቅንጅታዊ ስራ ክፈትት እንዳለበት በመጠቆም፣ በቀረጥ እና ከቀረጥ ነጻ ከውጭ የሚገቡ የፍጆታ ምርቶች ገበያ ላይ ዋጋቸው ተመሳሰይ መሆኑን በውይይቱ አንስተዋል፡፡
    በህጋዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ አስመጭ እና ላኪ ነጋዴዎች መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
    የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር የውጭ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሀድጎ በበኩላቸው በንግዱ ዘርፍ ያለው ቅንጅታዊ ስራ ከፈተት እንዳለበት በማመላከት የህገ ወጥ ንግድ የሚፈታተን እና ለመቀጣጠር አዳጋች ተግባር መሆኑን ገልጸው ፤ የቁጥጥር ስራውን ለመጠናከር ቅኝት እየተደረገ ህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ አንደሚገባ መፍትሄ አመላክተዋል፡፡
    የቋሚ ኮሚቴው አባልት በበኩላቸው ህገ ወጥ ንግዱን ለማስቆም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በቅንጀት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለህጋዊ ነጋዴዎች እና ለአምራች ኢንዱስተሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል ።
    የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጀዋር በንግድ ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሰራር ማነቆዎችን እና ህገወጥ ንግዱን በጋራ ለመከላከል ቢሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የባለድርሻ አካልተ ተሳትፎ እና የኮሚቴው ድጋፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ሲል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኮሚኒኬሽን ዘግቡዋል።