በሶማሌ ላንድ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ አብዱላሂ አብዱረህማንን ጨምሮ የሶማሌ ላንድ የንግድ ዘርፍ አመራሮች ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ጋር ውይይትና ጉብኝት አድርገዋል ። ከሶማሌ ላንድ ወደ ድሬዳዋ የመጡት አመራሮች በተለይም በድሬዳዋ ውስጥ ያለውን ምቹ ኢንቨስትመንት በማየት በቀጣይም በሱማሌ ላንድ የሚገኙ ባለሀብቶች ድሬዳዋ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማድረግ ያለመ ነው ።
የሶማሌላንድ ባለሀብቶች ድሬዳዋ ላይ ኢንቨስት ያደርጉ ዘንድም ከመሬት አቅርቦት ፣ ከኢንዱስትሪያል ፓርክ እንዲሁም ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ለአመራሮቹ በማሳየትና በማስጎብኘት የሶማሌ ላንድ ባለሀብቶችን ወደ ድሬዳዋ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለመጋበዝ መሆኑን ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ተናግረዋል ።
እንደሚታወቀው በከተማችን ድሬዳዋ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ላይ ካለው የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የግብአት እጥረት ችግር ጋር ተያይዞ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይቻል ዘንድ እንደሚሰራና በቀጣይም በክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር የሚመራ የአመራር ቡድን ሶማሌ ላንድ በመሄድና ባለሀብቶቹን በድሬዳዋ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመጋበዝ ይቻል ዘንድ በቀጣይ እቅድ መያዙንም ነው አቶ ሀርቢ ቡህ የተናገሩት ።
የሶማሌ ላንድ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስተር የሆኑት አቶ አብዱላሂ አብዱረህማን በበኩላቸው ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር የተለያዩ የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉ ገልፀው በቀጣይም በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አምራሮችም በቀጣይም ወደ ሶማሌ ላንድ እንዲመጡም ጋብዘዋል ።
የሶማሌ ላንድ ከፍተኛ አመራሮችም የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ ሬድስታር ፣ የሸሙ ፋብሪካ ፣ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ላይ በመዟዟር በከተማዋ ላይ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴዎች ጉብኝት አድርገዋል ።


