የሁለተኛው ምእራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብርም በዛሬው እለት ተካሂዷል።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወገኖቻችንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታወቃል ከዚሁ ጋር ተያይዞም በድሬዳዋ አስተዳደሩ ይኸው ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምእራፍ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በርካታ የአስተዳደሩን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ። በዛሬው እለትም የሁለተኛው ምእራፍ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሂዷል።
በዚሁ መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የከተማ መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ\ሮ ጫልቱ ሳኒ በኢትዮጲያ መንግስትና በአለም ባንክ መካከል በተደረሰ ስምምነት በተመረጡ 83 ከተሞች እንዲሰፋ የተደረገው 2 ተኛው ምእራፍ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት ትግበራን ለማስጀመርና በነባሩ ፕሮጀክት የተገነቡ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመመረቅ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረው ይኸውም ፕሮጀክት ጊዜ በማይሰጠው ፍፁም ድህነት ውስጥ ላሉና አስታዋሽ አተው በህይወት ከሞት ጋር ትንቅንቅ ለገጠሙ ትልቅ ተስፋ ሆኖ የቆየና ለብዙዎች እናቶችና ህፃናት እንዲሁም ጧሪ ላጡ አረጋዊያንና ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚኖሩ የከተማ ነዋሪዎቻችን ትልቅ ከለላ የሰጠ ፕሮግራም መሆኑን ወ\ሮ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል።
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የከተማ ዜጎችን የምግብ ዋስትና አላማን በማንገብ ያለፍትን አምስት አመታት 11 ከተሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሰራበት የነበረ ፕሮጀክት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው ከነዚህ ከተሞች ውስጥም የድሬዳዋ አስተዳደር አንዱ እንደሆነና በአስተዳደሩ በሚገኙ 9 ቀበሌዎች በየአመቱ 3 ቀበሌዎችን ተጠቃሚ በማድረግ በሶስት ዙር ሁሉንም ቀበሌዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ነው አቶ ከድር ጁሀር በመርሀ-ግብሩ ላይ የተናገሩት ።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የዜጎቻችንን ህይወት የታደገና እየታደገ ያለ ፕሮጀክት እንደሆነና ባለፍት አምስት አመታት በአካባቢ ልማት ስራዎች ሆነ በቋሚ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑ ቁጥራቸው ከ 600 ሺህ በላይ የሆኑ ዜጎችን የእለት ጉርስ ማሟላትና የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ማስቻሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወ\ሮ አየለች እሸቴ ተ ተግረዋል ።
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ በማሻሻልና በመለወጥ ረገድ አይነተኛ ፈይዳ እየተጫወተ ያለ ውጤታማ ፕሮጀክት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሮቤል ጌታቸው ተናግረው የአስተዳደራችን ነዋሪዎች የጥቅሙ ተቋዳሽ ከሆኑም እነሆ 5 አመት የሆናቸው ሲሆን ፕሮጀክቱም በመጀመሪያው ምእራፍ ከ 2009 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም ባሉት አመታት ውስጥ በሶስት ዙሮች 43.610 የአስተዳደራችንን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ነው አቶ ሮቤል ጌታቸው የተናገሩት ።
በመርሀ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይም ሶስተኛ ዙር ከፍተኛ ቁጠባ ለቆጠቡ አካላት እንዲሁም ለከተማ ፣ ለክልሎች እንዲሁም ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የተለያዩ ሽልማቶችን ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ የተቀበሉ ሲሆን የፅዳት ዘመቻ ፣ የቢል ቦርድ ምርቃት ፣ በሴፍቲኔት የተሰራ ትምህርት ቤት ምርቃትና ጉብኝት መርሀ-ግብሮች ተካሂደዋል ።


