የ6.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአሰሊሶ ገጠር ቀበሌ ጥርጊያ መንገድ በሁለት ቀን ውስጥ ይጠናቀቃል ::

    የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን በዘጠና ቀን እቅድ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታ ጥገናና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሲን አህመድ ተናገሩ፡፡
    ከነዚህ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ውስጥ የአሰሊሶ ገጠር ቀበሌ የመንገድ ስራ ይገኝበታል ያሉት ዳይሬክተሩ አሰሊሶን ከሁላሁሉል የሚያገናኝ የጥርጊያ መንገድ እንዲሁም እስከ ለገኦዳ መሄድ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
    ግንባታው በባለ ስልጣን መስሪያ ቤቱ በራሱ አቅም ያከናወነው ሲሆን አጠቃላይ የ6.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 15 ሜትር የጎን ስፋት አለው ተብሏል፡፡ ለግንባታ ስራው ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያሶጣ የነበረው ፕሮጀክት ግንባታው በባለ ስልጣን መስሪያ ቤቱ በራሱ አቅም በማከናወኑ ለሌላ ወጪ እንዳይዳረግ ረድቶታል ብለዋል፡፡
    ከዚህ ቀደም መንገዱ አስቸጋሪ እና ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት መኪና ማንቀሳቀስ እንደሚያስቸግር አቶ ያሲን ጠቅሰዋል፡፡ ከኢዱስትሪ ፓርክ ጋር ተያይዞ ሰራተኛችን ማመላለስ በመንገዱ ያስቸግር እንደነበርም አንስተዋል፡፡
    ዝናብ ከዘነበ የገጠሩ ማህበረሰብ ወደ ከተማ በመውጣት መገበያትም ሆነ ምርቱን ማድረስ ይቸገር የነበረው መንገድ በዘጠና ቀን እቅዳችን ውስጥ ይህን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
    መንገዶች ባለስልጣን የሚሰራቸው መንገዶች የትራፊክ ፍሰት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው ያሉት አቶ ያሲን ይህ የአሰሊሶ የመንገድ ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ መሰል የልማት ስራዎች በጀልዴሳ፣ ሁሉልአዩ፣ መልካ ቀሮ፣ ደበሌ፣ የገጠር ቀበሌዎች ላይ ተመሳሳይ የመንገድ ስራ ግንባታው እንደሚቀጥል መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታ ጥገናና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሲን አህመድ ገልፀዋል፡፡
    በህብረተሰቡ የሚነሱ የመንገድ ተደራሽነት ችግርን በመቅረፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ90 ቀን እቅድ አቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጸው ተቋሙ በየደረጃው የሚነሱ የመንገድ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ማግኘት እንዲችሉ ማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ላይ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡