በከተማም በገጠርም እየተሰሩ ያሉ የመንገድ የልማት ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሰፊው እየተሰሩ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን ሀላፊ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ተናገሩ፡፡
እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ ለበርካታ ጊዜያት በህዝብ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በአፋጠኝ የመጨረስ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በዘጠና ቀን እቅድ ውስጥ በማካተት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በመንገዶች ባለስልጣን የተያዙ ነባር ፕሮጀክቶች የ4.2 ኪ.ሜ የድሮ ኬላ የመንገድ ስራ፣ የ5.4 የገንደ ተስፋ የመንገድ ስራ፣ የቦረን እና የሲስታ መንገድ የከፈታ ስራዎች የዘገዩ ቢሆኑም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሊጓተቱ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በዘጠና ቀን እቅዳችን ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለን የያዝናቸው የህዝብ እሮሮ የሆኑ መንገዶችን የማስተካከል፣ አራት ነባር ድልድዮችን የማስዋብና የመጠገን፣ ድልድይ ስር ያሉ የጎርፍ መከላከያ መውረጃዎችን የማጠናከር ስራ ተሰርተው መገባደጃ ላይ መሆናቸውን አቶ ብሩክ ገልፀዋል፡፡ የሶላር መብራቶችም በዋና ዋና የከተማው ቦታዎች ላይ መተከላቸውን ተናግረዋል፡፡
በየቦታው በከተማው ውስጥ ተቆፋፍሮ የሚታየው ከተማዋን በሁሉም መንገድ የማልማት እና የመቀየር ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከነዚህ ስራዎች ውስጥ የእግረኛ መንገድ በሰፊው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የመንገዶች ባለስልጣን ሀላፊው የተናገሩት፡፡
ከሀይስኩል ትምህርት ቤት እስከ ዲፖ ገበያ የእግረኛ መንገድ የሸክላ ንጣፍ የተሰራ ሲሆን፣ ከለንበርዋን ፍርድቤት ፋይናንስን አልፎ እስከ መብራቱ ድረስ የሚሰራው የሸክላ ንጣፍ የእግረኛ መንገድ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ብሩክ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ ወደ ማህል ከተማ ውስጥ በመግባት በሳቢያን፣ በገንደቆሬ በመሳሰሉ አካባቢዎች ላይ የእግረኛ መንገዶችን የማስዋብ እና የሸክላ ንጣፍ ስራዎችን ለማከናወን በእቅድ ይዘናል ብለዋል፡፡
ሌላው የትራፊክ ምልክቶችን አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ላይ በማስቀመጥ የፍጥነት መቀነሻ ብርሃን ሰጪ የሆኑንት አስር የተመረጡ ቦታዎች ላይ አስተክለናል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የትራፊክ ምልክቶች በትምህርት ቤት አካባቢ፣ በሆስፒታሎች መዳረሻ ላይ ምልክቶቹ መተከላቸውን አቶ ብሩክ ተናግረዋል፡፡
ከኮብል እስቶን እጣፍ ጋር በተያያዘ ሰፊ ስራዎች መስራታቸውን የጠቀሱት አቶ ብሩክ በሁሉም ቀበሌዎች ስልሳ ዘጠኝ ማህበራትን የስራ እድል ማመቻቸታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከማህበራቱ ጋር ቀደም ብለው የስራ ውል የተፈራረሙ ሲሆን ስራዎችን የሚያጓትቱ እና የጥራት ደረጃው የወረደ ስራ የሚሰሩ ማህበራት ላይ በባለሙያ አስገምግመን ክፍያ የማንፈፅም መሆኑን ቀድመን ለማህበራቱ አሳውቀናል ብለዋል፡፡
በከተማ ደረጃ ሰፊ መነቃቃትን የፈጠረ ውጤት እያመጣን ያለንበት የመንገድ ልማት ስራዎች ቀጣይነት ያላቸው ተግባሮች ናቸው ብለዋል አቶ ብሩክ፡፡ በህዝብ ዘንድ ትልቅ እሮሮ የነበሩ የዘመናት ጥያቄ የሆኑ በዚህ ዘጠና ቀናት ውስጥ እየተሰሩ እንዳለና አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የተገለጸ ሲሆን በበጀት መደገፍ ስላለባቸው በቀጣይ የምንሰራቸው ይሆናሉ ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በገጠር በእቅድ ደረጃ 80 ኪ.ሜ የመንገድ ከፈታ እና የጥርጊያ ስራ ለመስራት ታቅዶ መጀመሩን የመንገዶች ባለስልጣን ሀላፊ አቶ ብሩክ የተናገሩ ሲሆን በዚህ ዓመት 15 ኪ.ሜ የመንገድ ከፈታ እና የጥርጊያ ስራ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በዋናነት ሶስት የገጠር ቀበሌዎችን ይዘን እየሰራን ሲሆን ዋሂል፣ ኮርቱ፣ ጀሎ በሊና ላይ ቦታዎችን የማስተካከል ስራዎች እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡


