በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል በሪፎርሙ/በለውጥ ሥራው በተፈፀሙ ተግባራት በአገልግሎት አሰጣጥና በሌሎችም መስኮች መሻሻሎች እየታዩ መሆኑ ተገለፀ፡፡

    የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙና ኢብራሂም በሆስፒታሉ ለበርካታ ጊዜያት በህብረተሰቡ ሲነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎችም ጥያቄዎች ሪፎርሙ/የለውጥ ሥራው ከተጀመረ ወዲህ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆኑንና በአገልግሎት አሰጣጥና በሌሎችም መስኮች መሻሻሎች እየተዩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
    ○አሠራር ላይ ከተገኙ ለውጦች አንፃር በሆስፒታሉ በሪፎርሙ/በለውጥ ሥራው ሂደት በኦፕሬሽን/ ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ወደ ሥራ ያልገቡ ባዶ ክፍሎችን በማደስና የህክምና ግብዓቶችን በማሟላት ብሎም ተጨማሪ ባለሞያዎችን በመመደብ ወደ ሐረርና አዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን የሪፈራል ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ከመቻሉም በላይ በየዕለቱ ይሠሩ የነበሩ የቀዶ ጥና ሥራዎችን በብዙ እጥፍ መጨመር መቻሉን
    ○የመልካም አስተዳደርና የካይዝን ትግበራን በተመለከተ በሁሉም የሥራ ክፍሎች አገልግሎት የማይሠጡ የህክምና መሳሪያና ሌሎችም ቁሳቁሶች የተለዩ ሲሆን ጊቢውን የማስዋብና ፅዱና ምቹ የማድረግ ሥራዎች የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኝ ከመሆኑም ባሻገር የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅቶች እየተደረጉና በሆስፒታሉ ያልነበረ የሲቲ እስካን ግዢን በመፈፀም ወደ አገልግሎት በማስገባትና X-ray/ኤክስሬ ወይም ራጅ በመጨመር ተገልጋዩ በሆስፒታሉ ውስጥ እነዚህን አገልግሎቶች እንዲያገኝ በማስቻል ያለበትን ወጪ መቀነስ መቻሉን
    ○እንዲሁም ከሰው ሃብት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለሁሉም የሆስፒታሉ ሠራተኞች የሥራ ድርሻ ዝርዝር ተሰጥቶ በተሰጠው የሥራ ዝርዝር መሰረት እየተሠራ ሲሆን በሆስፒታሉ አመራሮችና በሪፎርሙ/ የለውጥ ሥራ ኮሚቴዎች ድጋፍና ክትትልም እየተደረገ እንደሆነ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡
    ሥራ አስኪያጇ ጨምረውም ሪፎርሙን/የለውጥ ሥራዎች መጀመርን ተከትሎ በተሠሩ ሥራዎች ሁሉም የሥራ ክፍሎች መነቃቃትና የተሻለ አፈፃፀም እየታየባቸው መሆኑን እና በቀጣይም ሪፎርሙ/የለውጥ ሥራው የሚጠይቀውን ተግባራት ከዚህም በተሻለ በማከናወን የተገልጋዮቻቸውን እርካታ ለመጨመር ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡