የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በሚንስትሮች ምክር ቤት በወጣው የነዳጅ ድጎማ ደንብ ዙሪያ ከነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ፣በትራንስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ አሽከርካሪዎች እና ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል ፡፡
የውይይት መድረኩ በነዳጅ ድጎማ ደንብ ዙሪያ ፣የአፈጻጸም መመሪያዎች እና በተዘጋጁ የአሰራር መተግበሪያ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው፡፡ በመድረኩም በሚንስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የነዳጅ ድጎማ ደንብ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የንግድ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሚኑ ጣሀ እንደገለጹት የነዳጅ ድጎማ ስርአቱን በአዲስ መልክ ተከልሶ ድጎማ የሚያስፈልጋቸውን ብቻ በመለየት ማስተካከያ የተደረገ መሆኑን ገልጸው በዚህም በነዳጅ ድጎማ ውስጥ የሚካተቱት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልገሎት ሰጪዎች ፣ለመደበኛ አገር አቋራጭ ትራንስፖርት የመጫን አቅማቸው ከ12 እስከ 47 የሆኑ እና መለስተኛ አውቶብስ ሲሆን የግል (የቤት ) እና የመንግስት መኪኖች ድጎማው የማያካትት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በድጎማው የሚካተቱ የነዳጅ ውጤቶችም ቤንዚን ፣ናፍጣ እና ኬሮሲን ብቻ መሆናቸውንም ገልጸው የድጎማውም ጊዜ ገደብ ለ5 አመታት የሚቆይ እና ተፈጻሚነቱም ከመጪው ሀምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ሀላፊው አስረድተዋል፡፡
የፌደራል ትንስፖርት ና ሎጅስቲክ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተሸከርካሪ ዳይሬክቶሬት አቶ አለማየሁ ብርሃኑ በበኩላቸው የነዳጅ ድጎማው በነዳጅ አጠቃቀም እና አሰራሮችን በማሻሻል ቀልጣፋ አሰራር ስርአትን በመዘርጋ መልካም ጅማሮዎች ያሉ መሆኑን ገልጸው በነዳጅ ድጎማው እስከ አሁን 5015 (አምስት ሺ አስራ አምስት) ተሸከርካሪዎች የተመዘገቡ እና በመመዝገብ ላይም መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አክለውም የድጎማውን አገልግሎት የሚያገኙትም በቴሌ ብር የአሰራር ሲስተም ውስጥ የተመዘገቡ ብቻ መሆናቸውን ተናግረው የተመዘገቡ ተሸከርካሪዎችም የመለያ ምልክት የሚለጠፍባቸው ሲሆን ያልተመዘገቡ ድጎማውን የማያገኙ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ለማ እንደገለጹት በሀገራችን በርካታ ተቋማት በቴሌ ብር አማካኝነት ትልልቅ ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንዲሁም የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ግብይት እንደሚፈጽሙ ገልጸው ግብይቱ በኤሌክትሮኒክስ አማካኝነት የሚደረግ ግብይት ሲሆን በነዳጅ ድጎማ በሚደረገው የግብይት ሰርአትም አሰራሩን ይበልጥ ቀልጣፋ እና ፈጣን በሆነ መንገድ ለመተግበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው በቴሌ ብር መተግበሪያዎች ዙሪያም ሀላፊው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀረቡት የነዳጅ ድጎማ ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየት ሰጥተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡


