ዛሬ ሀምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ለክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር በስሙ ፓርክ መሰየሙን የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር አብስረዋል፡፡
ክቡር ከንቲባ ከድር በቦታው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በአገራችን የሙዚቃ ስራ ውስጥ እንደተወደደ እና እንደተከበረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ታዋቂ ሆኖ የኖረውን ታላቁ የሙዚቃና የፍቅር ሰው ለክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ መታሰቢያ ለመሰየም በመገኘቴ ከልብ የመነጨ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡
ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር የምስራቅ ኢትዮጵያ ፈርጥ በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ ተወልዶ፣ አድጎና ከሙዚቃ ተዋውቆ ለአገር የተረፈ አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያ ነው ሲሉ ክቡር ከንቲባ ከድር ተናግረዋል፡፡
እንደ ክቡር ከንቲባ ከድር ገለፃ ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር የኦሮምኛ ቋንቋ ድምፃዊ ይሁን እንጂ የሚዘፍነው ለኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ናት የሚለውን ብሂል በሚያሳይ መልኩ ሙዚቃዎቹ ኦሮምኛን ፈፅመው በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ሁሉ የተወደዱ ናቸው ብለዋል፡፡
የሀቅ፣ የመብት፣ የሰላም፣ የበጎ ነገር ታጋይ ነኝ በማለት ራሱን የሚገልፀው ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር ለህዝብ ነፃነትና እኩልነት መከበር እድሜ ልኩን በመታገል በጎ ተፅህኖ ማሳደር የቻለ የህዝብ ልጅ መሆኑ በመድረኩ ተነግሯል፡፡
በመጨረሻም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ክንቲባ ፅ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ፓርክ ከዛሬ ጀምሮ አሊ ቢራ ፓርክ ተብሎ በስሙ መሰየሙን በታላቅ ክብርና ከልብ የመነጨ ደስታ መሰማታቸውን በራሳቸውና በድሬዳዋ ህዝብ ስም አብስረዋል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ጨምሮ፣ ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር፣ ከክብርት ሚስስ ሊሊ ማርቆስ ክቡር አርቲስት አሊ ቢራ ዶ/ር ባለቤት፣ ክብርት ፈቲያ አደን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የኢፌዲሪ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ አምባሳደር መሀመድ ድሪር፣ ክቡር አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፅ/ቤት ሀላፊ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ትውልደ ኢትዮጲያዊያን የድሬዳዋ ልጆች፣ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ታድመዋል፡፡


