በአስተዳደራችን ከ 1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ በድሬዳዋ ከተማ ከ 1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።

    በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር አዲስ መንግስት ከተመሰረተ ወዲህ መንግስት በገባው ቃል መሰረት በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ክቡር ከንቲባ ከድር ተናግረዋል፡፡
    በዚህ አመት በገጠርም በከተማም 31 ፕሮጀክቶች የሚመረቁ ሲሆን ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ 1.220.109.861 ብር ወጪ መደረጉን ክቡር ከንቲባው ገልፀዋል፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ 21 ፕሮጀክቶች በከተማ ውስጥ ሲሆኑ ከ 1.091.893.773 ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ከ 200 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ቀሪው 10ሩ ፕሮጀክቶች በገጠር ሲሆኑ 128.216.088 ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን ከ 35.652 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ክቡር ከንቲባው ተነግሯል፡፡
    የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ የአስተዳደራችን ልማት ላይ ከፍተኛ ፋይዳ ያኖረዋል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሱልጣን አሊዪ ናቸው፡፡ ዛሬ የሚመረቁ ፕሮጀችቶች ከወትሮው በተለየ መልኩ ግብዓት ተሟልቶላቸው እና ከተጠናቀቁ በኋላ ወደ አገልግሎት መግባት የሚችሉ ፕሮጀክቶች ብቻ ተመርጠው በመርሃ ግብሩ እንዲካተቱ የተደረጉ መሆኑን አቶ ሱልጣን አብራርተዋል፡፡
    በቀጣይ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በ2015 በጀት ዓመት እንዲጠናቀቁ በትኩረት የሚሰራ ይሆናልም ተብሏል፡፡ እንደ ሌላው ጊዜ 80% ወይንም 90% አፈጻፀም ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የዚህ መርሀ ግብር አካል ሆነው ያልተወሰዱ መሆኑን አቶ ሱልጣን ተናግረዋል፡፡
    አቶ ሱልጣን አክለውም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ከምረቃው በኋላ የአስተዳደራችን ነዋሪ በባለቤትነት ወስዶ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ፤ የወጣባቸውን ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ በተቋማቸው ስም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
    ክቡር ከንቲባው ከድር ጁሃር በማጠቃለያ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስተዳደራችን ያላትን ከፍተኛ የመልማት እድል እና ተስፋዎች በፌደራል መንግስትና በአስተዳደሩ ቅንጅት የተከናወኑ ስራዎችን ጠቅሰዋል፡፡ የአስተዳደራችን ምልክት የሆነው የድሬዳዋ ምድር ባቡር በአስተዳደራችን እንዲተዳደር መደረጉን ተናግረዋል፡፡
    ሌላው የነጻ የንግድ ዞን በቅርቡ እውን ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ክቡር ከንቲባው የደረቅ ወደብ ስራው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ በ3 ኪሎ ገብቶ በኢንደስትሪ ፓርክ የሚወጣ ቀለበት መንገድ ስራው ተጀምሮ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡
    እነዚህ በፌደራል መንግስት እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ እና ከተጠናቀቀው ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ተደምሮ የድሬዳዋ ብልፅግና በቅርቡ እውን የሚሆን መሆኑን ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር በመድረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡
    ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማስፋፊያ ሕንጻዎች፣ የስራ አመራር ካይዘን ኢንስቲትዩት ህንጻ፣ 358 የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ መንደር ጤና ጣቢያ፣ የማኑፋክቸሪንግ ሼዶች ግንባታ 1 እና 2፣ ጥቃት ለደረሰባቸው የህጻናትና የሴቶች ማገገሚያ ማዕከል፣ የጎሮ መጠጥ ውሀ፣ የሳኒቴሽን ፕሮጀክት፣ የሀፍካት ቁጥር 2 ድልድይ ግንባታ፣ የCT Scan አገልግሎት፣ የድልጮራ የማህበረሰብ ፋርማሲ፣ የመድሀኒያለም ት/ቤት ማስፋፊያ ተመርቀዋል፡፡
    በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ጨምሮ፣ ክብርት ፈቲያ አደን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሱልጣን አሊዪ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞች፣ አባ ገዳዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።