የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

    ከንቲባዉ ይህን ያሉት ዛሬ በገጠር ቀበሌዎች በተካሄደዉ የልማት ፕሮጀግቶች ምረቃ መረሃግብር ላይ ነዉ
    የገጠሩን ህብረተሰብ ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ከ128 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች በአሰተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የአከባቢዉ መህበረሰብ በተገኙበት ተመሪቀዋል ።
    የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈቲያ አደን እንዲሁም የካቢኔ አባላትን ያካተተው ቡድን በከተማ እና በገጠር ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችን በመመረቅ ላይ ናቸው።
    የዚሁ አካል የሆነው እና በገጠር ከ128 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ 10 ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
    ከፕሮጀክቶቹ መካከል ከ130 ሄክታር መሬት በላይ ማልማት የሚችሉ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀከቶች ፤የመጠጥ ዉሃ፣የጠጠር መንገድ እና የአሰሊሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ናቸው።
    በፕሮጀክቶቹ ምርቃት ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት በገጠሩ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
    በተለይ ካለፉት አመታት ወዲህ የገጠሩን ህብረተሰብ የማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ችግሮችን ለማቃለልና የገጠሩን ወጣት የስራ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት መሠረታዊ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
    ፕሮጀክቶቹ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ህብረተሰቡ ጥበቃ እና ክብካቤ ማድረግን ለአፍታ መዘንጋት እንደሌለበትም አሳስበዋል
    የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃ ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው የተመረቁት ፕሮጀክቶች የገጠሩን ህብረተሰብ ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነዉ የገለጹት።
    ያነጋገርናቸዉ አንድ አንድ የአከባቢዉ ነዋሪዎች በተሰራላቸዉ የልማት ፕሮጀግቶች የግብርና ስራቸዉን ከማገዝ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለዉ በመሆኑ መደሰታቸዉን በመግለጽ አሰተዳደሩን አመስግነዋል ።