የድሬዳዋ አስተዳደር የ2015 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ

    የድሬደዋ አስተዳደር ምክር-ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 1ኛ አመት ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስተዳደሩ የ2015 በጀት አመት የካፒታል ፕሮጀክቶች ረቂቅ በጀትና የመደበኛ በጀት በተከበሩ አቶ ሱልጣን አሊይ ለድሬደዋ አስተዳደር ምክር-ቤት ቀርቦ በምክር-ቤቱ የበጀት ኢኮኖሚ ንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት በተከበሩ ወ/ሮ አይናለም ተዘራ ምክረ ሀሳብ ከቀረበበት በኋላ በምክር-ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄ በተከበሩ አቶ ሱልጣን አሊይ መልስ ተሰጥቶበት የድሬደዋ አስተዳደር የ2015 ዓ.ም በጀት 5 ነጥብ 7 ቢሊየን በመሆን ፀድቋል፡፡
    በመቀጠልም የድሬደዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ላይ ከምክር ቤት አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከተነሱበት በኋላ ጥናቱን ካጠኑት አካላት አቶ ሰብስቤ መኮንንና የተከበሩ አቶ አብዱሰላም መሀመድ መልስ ሰተውበት የድሬደዋ አስተዳደር ቻርተር በቀጣይ ለሚመለከተው አካል ዳብሮ እንደሚላክ የተከበሩ ወ/ሮ ፈትሂያ አደን ገልፀዋል፡፡
    በመጨረሻም የድሬደዋ አስተዳደር የብልፅግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት የተከበሩ አቶ ደረጀ ፀጋዬ በተጓደሉ የድሬደዋ አስተዳደር የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት በእጩነት የተከበሩ ወ/ሮ ከሪማ አሊ፤የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍንና የተከበሩ አቶ ማርቆስ ባዩን ያቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት እጩዎችም ሁለቱ ቃለ መሀላ የፈፀሙ ሲሆን በእለቱ ያልተገኙ እጩ በውክልና ቃለ መሀላ እንዲፈፅሙ የምክር ቤቱ አባላት ለምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ውክልና በመስጠት የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 1ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በዚሁ ተጠናቋል፡፡