የትራንስፖርት አና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ከክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር የዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም ገመገመ::

    ቢሾፍቱ ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም፡ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር እና የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻፀም የክልል ትራንስፖርት ቢሮና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የተገኙ ተወካዮች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
    የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ በበጀት ዓመቱ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎትን ማሳደግ የትራፊክ ኮምፕሌስ እና የጭነት ተርሚናል ግንባታ የገጠር የትራንስፖርት አገልግሎት ሽፋን የማሳደግ፤ለጭነት ተሸከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን የሚያቋርጠውን 12 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን የባቡር መስመር ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ህብረተሰቡን በማወያየት የባለቤትን ስሜት መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል፡፡ የታለመለነት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች የድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚልፅ ስቲከር ለጥፈው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ስኬታማ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
    የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ላተሞ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የመንገድ ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታዎችና አግልግሎትን ማሳደግ እንዲሁም የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የግንዛቤ ስራዎችን በመስራት የተከናወኑ ዝርዝር ጉዳዮችን አመላክተዋል፡፡
    የ2014 በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት የአማራና፣ ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን በመዘርዘር የተወሰዱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችንና ቀጠያ ትኩረት የሚሹ ሃሳቦችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
    የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ውቤ አጠናፉ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በክልሉ የአሽከርካሪዎችና የቴክኒሻን ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መስጠት እና ማደስ አገልግሎት፣ የህዝብና የከተማ ትራንስፖርት ወቅታዊና መደበኛ የትራንስፖርት ታሪፍ ተጠንቶ ተግባራዊ መደረጉ፤አመቱ በተለያዩ ከተሞች ትራፊክ ኮምፕሌክስ ኔትወርክ ዝርጋታ ስራ መከናወኑን፣የትራንስፖርት አገልግሎትን ማስፋፋት እና ተደራሽ ከማድረግ አንፃር የከተማ ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች መርሃ ግብር እንዲሰሩ መደረጉን፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በርካታ የግንዛቤ ስራዎች መሠራታቸውንና ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
    የ2014 በጀት አመትን ሪፖርት በዝርዝር የገመገመው መድረኩ ዘንድሮ ተግባራዊ የሆነው የታለመለት የነዳጅ ድጎማን በተመለከተ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በአተገባበሩ ላይ የነበራቸውን ሚና በተመለከተ እንዲሁም ያገጠሙ ክፍተቶችን እና የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን በተመለከተ አቶ አብዱልበር ሸምሱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
    መድረኩን የመሩት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በ2014 በጀት ዓመት የዘርፉ አመራርና ሰራተኞች በነበራቸው ቁርጠኝነት ከባድና ሊፈፀሙ የማይችሉ ስራዎችን መፈፀም መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በጀመርነው ልክ በቁርጠኝነት መስራታችንን በማጠናከር ቀጣይ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡ በድሬደዋ ከተማ የሚቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጠናን በማስፋት በቀጣይ በተለዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚተገበር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሎጂስቲክስ አፈፃፀማችን ሲመዘን አበረታች መሆኑን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሎጂስቲክ አንፃር ሰፊ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
    ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ መናህሪያዎችን ከማዘመን እና ደረጃዎችን ከማውጣት አንፃር እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች በመልካም አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ መገምገሙንና ክልሎና ከተማ አስተዳደሮች በጀመሩት ልክ ጥራት ላይ ትኩት በማድረግ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
    ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሃሰን በበኩላቸው ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከርና ክልሎች እርስ በርስ የሚኖራቸውን ትስስር ይበልጥ በማጠናከር እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
    በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተገኙ የስራ ሃላሪዎች በዘርፉ ያሉ ችግሮችና መልካም እድሎችን በማንሳት ሰፊ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል
    ምንጭ:- የፌድራል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚ/ር ኮሙኒኬሽን ነዉ