የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የ 2014 በጀት አመት የማጠቃለያ ኮንፍረንስ አካሄደ ።

    በዛሬው እለት በኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የ 2014 በጀት አመት የማጠቃለያ ኮንፍረንስ በደመቀ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን በዚሁም መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የፓርቲዉ መዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የአሰተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የአሰተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የብልፅግና ፓርቲ በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አመራር የሚፈልቀው ህገ-መንግስታዊ በሆነ አግባብ በህዝብ ተመርጠው ስልጣን በሚይዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ መሆኑን ከመቀበሉም ባለፈ የመሪዎቹ ጥንካሬ የሚመዘነውም ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ቀጣይነት ያለውና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት በማረጋገጥ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባትና ቀጣይነቱን የማረጋገጥ ተልእኮን በአግባቡ የተወጡ እንደሆነ እንደሚያምን አቶ ከድር ጁሀር ተናግረዋል ።
    ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር አክለውም ብልፅግና ፓርቲ አመራሮቹና አባላቱ በተሰባሰቡበት አላማ ዙሪያ የአስተሳሰብ ግልፅነት እንዲይዙ ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታን መረዳትና መተንተንን እንዲያጎለብቱ ፣ የህዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች በቅደም ተከተል በመያዝ መፍታት እንዲችሉ ዲሞክራሲን የማሳደግና ፀረ ዲሞክራሲን የመዋጋት አመለካከትን እንዲያዳብሩ በተለያዩ ጊዜያት የአመራርና አባላት አቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝና በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን አቶ ከድር ጁሀር በእለቱ ተናግረዋል ።
    እንደ አስተዳደር በፖለቲካው መስክ ያስቀመጥናቸውን ግቦች ለማሳካት አመራሮችንና አባላትን እንዲሁም መላው የአስተዳደራችንን ደጋፊዎች በተደራጀ መልኩ በማስተባበር ያልተመለሱ የህዝብ ዋና ዋና ጥያቄዎችን በየደረጃው በመመለስና ህዝብን እያማረሩ ያሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ቁልፍ ጥያቄዎችን የመፍታት ብቃት ያላቸው ጠንካራ የአመራር ስምሪት በመስጠትና በየጊዜው የድጋፍና ክትትል በማድረግ በአስተዳደራችን ላይ ተጨባጭ ስኬቶችንና ውጤቶችንም እያስመዘገቡ እንደሚገኙ የፓርቲዉ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣የአሰተባባሪ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ እና የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ክቡር አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናግረዋል ።
    የ 2014 በጀት አመት የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሻኪር አህመድ ያቀረቡ ሲሆን የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የ 2014 ዓ.ም የፓርቲ ኮንፍረንስ ላይ ከቀረበው አመታዊ ሪፖርትና የቀጣይ አቅጣጫ በመነሳት በጋራ መግባባት ባለ12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መድረኩ ተጠናቋል ።
    በዛሬው እለት በኢትዮ-ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መስብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው መድረክ ላይም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ\ሮ ፈቲህያ አደን ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት ፣ የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮችና አባላት እንዲሁም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል ።
    በአለማየሁ አበበ ።
    ፎቶ :- በይድነቃቸው አብርሃም ።