ማጠቃላያ ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት በብልፅግና ፓርቲ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የድጋፍና ክትትል አስተባባሪዎች ሰብሳቢ አቶ ኬኪያ ድሪባ እንደገለጹት ኮንፈረንሱ ፓርቲዉ በብዙ ስኬቶች በታጀበበት ወቅት ላይ መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰው በተለይ እንደ ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ከአባላት እስከ ከፍተኛ አመራሩ በተደረገ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስኬታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ወደ ማኅበረሰቡን ከበፊቱ በበለጠ መድረስ እንዲያስችለው ያቋቋመው የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ፣ የመማር ማስተማር ስራውን ለማዘመን በ190 ሚሊየን ብር ያስገነባው የICT የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የዳታ ሴንተር የግንባታ ስራ እንዲሁም በአካዳሚክና በሰው ሀብት ልማት ዘርፍም የተሰሩት ስራዎች በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ከሆንባቸው ተግባራትን መካካል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ ሲባል ግን ከፍተቶችን የፈጠሩ ድክመቶችና ውስንነቶች አልነበሩም ማለት አይደለም ያሉት አቶ ኬኪያ በተለይ በያዝነው በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙት መላው የፓርቲው አመራሮችና አባላቱ ራሳቸው በቅተው ሌሎችን በማብቃት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አስራርን በመዋጋት ዩኒቨርሲቲው የሰነቀውን ርዕይን ማሳክት እንዲችል ርብርባቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የድሬደዋ የብልጽግና ፓርቲ የልማታዊ ተቋማት የእቅድ ዝግጅት ድጋፍና ክትትል ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኡመር አህመድ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬደዋ ፓርቲያችን በማኅበራዊው፣ በምጣኔ ሀብት በርካታ ድሎችን ማስመዝገብ የቻልንብት በፖለቲካው ዘርፍም የህዝብን ተሳትፎ ከቀድሞው በበለጠ ማሳደግ የቻልንብት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡ እነዚህ ስኬቶች ለማስቀጠልም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና አባላቱ የጀመሩትን አበረታች ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በኮንፈረንሱ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የብልፅግና ፓርቲ የ2014 የስራ አፈፀፀም ሪፖርትና የ2015 እቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በመጨረሻም የመሠረታዊ ድርጅት አመራርና የህዋስ አመራር ምርጫ ተደርጎ ተጠናቋል፡፡


