ከነሀሴ 11ጀምሮ በተለያዩ የክላስተሩ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ጋር ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ዙር የህዝብ ውክልና አወጣጥ የውይይት መድረክ የማጠቃለያ ስነ-ስረዓት በዛሬው እለት የክላስተሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።
በሽማግሌዎች ጸሎት(ዱዓ) በተጀመረው የውይይት መድረክ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲህያ አደን ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ ተወካይ የተከበሩ ዶ/ር ቢፍቱ መሀመድ እና የክላስተሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ተመራጮች የተገኙ ሲሆን ከክላስተሩ ነዋሪዎች ጋርም ገንቢ ውይይት አካሂደዋል።
በክላስተሩ የሚገኙ 12 ቀበሌዎች ነዋሪዎችም የቀበሌው ተመራጮች የነዋሪውን ድምጽ ለመስማት ወደ ህዝቡ በመውረዳቸው የተሰማቸውን ገልጸው በተወካዮቻቸው በኩል በየቀበሌያቸው የሚገኙና መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ያሉትን ከንጹህ መጠጥ እና ከመስኖ ውሀ ፣ ከመንገድ ፣ ከማብራት ፣ ከትምህርት ፣ ከኔትወርክ ጋር የተያያዙ እና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ አስተያየታቸውንና ጥያቄያቸው በዝርዝር አቅርበዋል ። በተነሱ ጥያቄዎች ላይም ጉዳዩ በሚመለከታቸው ቢሮዎች የሚሰሩ እና የክላስተሩ ተመራጮች የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ምላሽ ሰጥተውባቸው አብዛኞቹ በህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ግን በቀጣይ እንደ የቤት ስራ ተወስደው የሚሰራባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የተከበሩ አፈ-ጉባኤ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር በገጠር ክላስተሮች ለሚታየው ክፍተቶች ዋነኛ ምክንያት ለገጠሩ ማህበረሰብ ትኩረት አለመሠጠቱ ሳይሆን በቻርተሩ ከተደነገገው የበጀት ውስንነት ምክንያት የተፈጠሩ ውስንነቶችን መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም እስካሁን ሲካሄድ የቆየው ለከተማ ተብሎ የሚለቀቀውን ውስን በጀት አስተዳደሩ ለገጠር ቀበሌዎችም ጭምር እየተጠቀመ መሆኑን ጠቅሰው እነዚ አመታትን የተሻገሩ ጥያቄዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመለስ ቻርተሩን የማሻሻል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። ነገር ግን ትልቅ በጀት የማይጠይቁና በቀበሌ እና በማህበረሰብ አቅም ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎችን በመስራት የህዝቡን ልማት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ በተባበረ ክንድ መስራት እንደሚያስፈልግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፎቶ በፋዲል ሬድዋን
በ ከዲሱ ካሳ


