ድጋፉ ከአስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች እና አመራር እንዲሁም በገጠር ና በከተማ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ያዘጋጁት ሲሆን የእርድ ከብቶችና ሌሎች ቁሳቁሶችንም ያካተተ ነው።
አስተዳደሩ ለመከላከያ ሠራዊት ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የሰንጋና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት የብልጸግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደረጀ ጸጋዬ ናቸው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራም ማህበረሰቡ በደም ልገሳ በነቂስ የተሳሰተፈበት ፣ 68 ሰንጋዎችን ፣ 281 ፍየል ፣75 ኩንታል በሶ ፣ቆሎ ፣ሩዝ፣ፓስታ ፣ቴምር እንዲሁም በዛሬውም እለት በጥሬ ገንዘብ እና ሌሎች የአይነት ድጋፎች ከህብረተሰቡ እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ህዝብ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው በአሸባሪው ህውሃት የተከፈተብንን ጦርነት ለመቀልበስ ፊት ለፊት ውድ ህይወቱን እየከፈለ ያለውን ሰራዊት ለማበረታታት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርበዋል ፡፡
በተመሳሳይ የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ እና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ና ባለሙያዎች ከ70 ሺ ብር በላይ የሚገመት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የስንቅ ዝግጅት በማከናወን ላይ ናቸው።
ድጋፉ በከተማ ስራ አስኪያጅ ስር የሚገኙ መንገዶች ባለስልጣን ፣ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ፣ ቄራ አገልግሎት፣የነዋሪዎች እና የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ፣ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት እና ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን አመራር እና ሰራተኞች የተሰበሰበ መሆኑን የከተማ ስራ አሲኪያጅ ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ዑመር ድዋሌ ገልጸዋል ፡፡
ድጋፉ ከ70 ሺህ በሚበልጥ ወጪ የተዘጋጀ ጥራጥሬ፣ የዳቦ ዱቄት፣ በሶ፣ሲሆን ለሴት የሰራዊት አባላት የሚሆን የንፅህና መጠበቂያም በድጋፉ መካተቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አመራሩ እና ሰራተኛው ከወር ደሞዛቸው ለመከላከያ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ሀላፊው አንስተው ከሀገር የሚበልጥ ነገር ባለመኖሩ ሁሉም አካል ሀገር የማዳን ተልዕኮውን ቅድሚያ ሰጥቶ ሰራዊቱን እንዲደግፍም አሳስበዋል
በሌላ ዜና ለመከላከያ ሰራዊት ከ 400 ሺ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ የቀበሌ 06 አስተዳደር መድረጉን ያስታወቁት ደግሞ የቀበሌ 06 ምክትል ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቢፍቱ መሀመድ ናቸው።
በቀበሌው አስተዳደር መከላከያ ሰራዊቱን በማጀገን ረገድ ባሉት አደረጃጀቶች በርካታ ድጋፎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ገልጸው በአይነት ሩዝ ገብስ ፓስታ መኮረኒ ከማህበረሰቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
በሴቶች አደረጃጀት እየተዘጋጀ ያለው ይህ የስንቅ ድጋፍ ለሰራዊቱ አለኝታነት ማሳያ እንደሆነም ነው ሀላፊዋ ያነሱት ።
በስንቅ ዝግጅት ሲሳተፉ ያገኘናቸው የቀበሌው ነዋሪዎችም ሲገልጹ በወቅታዊ ሀገራችን ለህልውና ዘመቻ ከገንዘብ፣ከጉልበት ባሻገር የህይወት መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውንም በቁጭት በሞቀ የሀገራዊ ስሜት ተናግረዋል፡፡
በሰላም ለማ
ፎቶ፡- አብይ ሽመልስ


