የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ቢሮ እና የቢሮው ተጠሪ ተቋም የሆነው የድሬዳዋ ሥራ አመራር እና ካይዘን ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ተወያዩ። **

    የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ቢሮ እና የቢሮው ተጠሪ ተቋም የሆነው የድሬዳዋ ሥራ አመራር እና ካይዘን ኢንስቲትዩት አመራሮች እና ሠራተኞች ”ከሉዓላዊነታችን በተጻራሪ የቆመው የህወሃት ሸፍጥ ” በሚል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን የውይይቱ አላማም በአሸባሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ለ3ኛ ጊዜ የተከፈተው ጦርነት እና አሁን በድርድር ስም እየፈጠረ ያለው ውዥንብር መሰረተ ቢስ መሆኑን ለአመራሩ እና ለሠራተኛው ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።
    በውይይት መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይር ሀጂኑር እንደገለፁት አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፌድራል መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተው ሀገርን ለማፍረስ ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት ማወጁን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ጥምር ሀይላችን እየወሰዱ ያለውን የመከላከል እርምጃ መቋቋም ሲያቅተው የተለመደውን ሀሰተኛ መረጃዎች በማዘጋጀት እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሰራጨት የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
    አቶ ሀይር አክለውም የቢሮው አመራሮች እና ሠራተኞች የሽብር ቡድኑ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት በሀገር ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በአግባቡ በመረዳት እና ሁሉም በየፊናቸው ትክክለኛውን መረጃ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ እንዲሁም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በርትተው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
    የቢሮው አመራሮች እና ሠራተኞች በበኩላቸው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ያወጣውን ሀሰተኛ መግለጫ ከእውነት የራቀ እና አለም አቀፍ ባህበረሰቡን ለማደናገር አስቦ ያወጣው መሆኑን በማጋለጥ እና በማንኛውም ጊዜ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
    በተያያዘ ዜና የቢሮው አመራሮች እና ሠራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የደም ልገሳ ፕሮግራም አከናውነዋል።
    ምንጭ:- ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሙኒኬሽን