አቢሲኒያ ባንክ በድሬዳዋ ላይ ባሉት አጠቃላይ ቅርንጫፎች ለነዋሪው ህብረተሰብ ከሚሰጣቸው ቀልጣፋ የሆነ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በሰብአዊ ድጋፎች ላይም ቢሆን በንቃት በመሳተፍ በከተማዋ ላይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያቶች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ።
አቢሲኒያ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት በዛሬው እለትም በዲስትሪክት ፅህፈት ቤትና በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ቅርንጫፍ ሰራተኞቹን በማስተባበር ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ፣ ለአረጋዊያን የአስቤዛና የንፅህና መጠበቂያ እቃዎች እንዲሁም ለድሬዳዋ ደም ባንክ የደም ልገሳ መርሀ-ግብር አካሂዷል ።
በዚሁም የድጋፍ መርሀ-ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ወ\ሮ ሙሉካ መሀመድ የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው በእውቀት ታንፀው ያድጉ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋፆ መወጣት እንዳለባቸው ወ\ሮ ሙሉካ መሀመድ ተናግረው አቢሲኒያ ባንክ ያደረገው ተግባርም በእጅጉ የሚያስመሰግን እንደሆነም ገልፀዋል ።
አቢሲኒያ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት አቅመ-ደካማ ለሆኑና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች ያደረገው ድጋፍ በእጅጉ የሚያደስት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ኡመር አህመድ በመርሀ-ግብሩ ላይ ተናግረዋል ።
አቢሲኒያ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት በድሬዳዋ ላይ ባሉት 14 ቅርንጫፎች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችና አመራሮችን የዲስትሪክት ፅህፈት ቤትና አመራሮችን በማስተባበር አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚሆን የመማሪያ ቁሳቁስ ፣ የሀገር ባለ ውለታ ለሆኑና በዳዊት አረጋዊያን እንዲሁም በአሰገደች አረጋውያን ለሚገኙ እናቶችና አባቶች የአልባሳትና የምግብ ፍጆታዎች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያዎች በአጠቃላይ ከ 549 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ድጋፍ ከማድረጉም ባለፈ አንድም እናት በደም እጦት ምክንያት መሞት የለባትም በማለትና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ይሆን ዘንድም የደም ልገሳ መርሀ-ግብር እንዳካሄዱ የአቢሲኒያ ባንክ የድሬዳዋ ዲስትሪክት ቢዝነስ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አ\ቶ ተስፋሁን ሳህሉ ተናግረዋል ።
በዚሁም የድጋፍ መርሀ-ግብር ላይም ከፍተኛ የአስተዳደሩ አመራሮች ፣ የአቢሲኒያ ባንክ ሰራተኞችና አመራሮች ፣ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች ፣ አቅመ-ደካማ የሆኑ አረጋውያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
በአለማየሁ አበበ ።
ፎቶ :- በይድነቃቸው አብርሃም ።


